
አዲስ አበባ: መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቱሪዝም ሚኒስቴር አምስተኛውን ዓመታዊ የቱሪዝም ዘርፍ የጥናት እና ምርምር ኮንፈረንስ አካሂዷል።
ኢትዮጵያ የብዙ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ እንዲሁም የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ናት። የቱሪዝም ዘርፉን በጥናትና ምርምር በመደገፍ እና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ያላትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሠራም ነው። የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ የቱሪስት መስህቦችን በኅብረተሰቡ ዘንድ ትውውቅን፣ አንድነትን እና መከባበርን ለመፍጠር ልንጠቀምባቸው ይገባል ብለዋል።
ቱሪስቶች የሚኖራቸውን ቆይታ በማራዘም ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እና ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለዚህም መሠረተ ልማቶችን በማሟላት የምንሰጣቸውን አገልግሎቶች ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እንዲሁም ፍጹም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተሞለበት ማድረግ ይገባል ብለዋል። በቱሪዝም ዘርፉ የሚደረጉ ጥናት እና ምርምሮች ኢትዮጵያ ያሏትን የመስህብ ሃብቶች የለየ እና ትውልድ ተሻጋሪ እንደኾኑ መሥራት እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሯ አንስተዋል። በዕለቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ያላቸው ፋይዳ፤ በሆቴል ዘርፍ ላይ አረንጓዴ ልማትን ማጎልበት በተመለከተ፤ ዘላቂ የማኅበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ልማት ትስስሮች መኖር እና ሌሎችም ጥናታዊ ጽሑፎች ቀረበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሰላማዊት ነጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!