የቀይ ባሕር ጉዳይ ሲነሳ ግጭት የሚለው ከአእምሮ መውጣት አለበት።

41

ባሕር ዳር፡ መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ቀይ ባሕር እና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው የሚባለው እንዱሁ አይደለም የራሱ ሰፊ ምክንያቶች ስላሉት እንጂ። ይህ ወሳኝ የባሕር ክፍል ሲነሳ በቀጣናው ያለውን ትርምስ እና የቦታውን ወሳኝነት ማሰብ የግድ ነው።

ኢትዮጵያ ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት የነበራትን ገጽታ እና ቦታ ከፍ ያለ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል።

በተለይም የአውሮፓውያኑ ወረራ ባልጀመረበት በዚያ ዘመን ቀይ ባሕርን አሻግሮ ከማየት በዘለለ ለመቆጣጠርም ማንም ከልካይ አልነበራትም፤ የቀጣናው ዋና አጋፋሪም ነበረች። ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትገለል ለማድረግ ሴራው የሚጀምረው የጣሊያን ጦር በኤርትራ በኩል ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ካደረገው ወረራ ይመዘዛል።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ማለትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገችው ሙከራ አልሳካ ሲል እና በወቅቱ የኢትዮጵያን የአቅም ማጣት እንደ ዕድል የተጠቀመችው ጣሊያን ኤርትራ ላይ መሠረቷን ለመትከል ብዙ ስትጥር ቆይታለች።

ይሁን እንጂ ኤርትራ ላይ መሠረቱን አድርጎ የተቀመጠው ጣሊያን አልኾን ሲል እና ተሸንፎ ሲወጣ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመነጠል በርካታ ሴራዎችንም ሠርቷል።

አንደኛው ኤርትራን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን 1952 ላይ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀጥል አስወስኖም ነበር።

ይህም ሂደት ኢትዮጵያ የባሕር በሯ ጉዳይ አደጋ ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ምልክት እየሰጠ ነበር ማለት ይቻላል።

ረጅም ዕድሜ ያላስቆጠረው የኤርትራ በፌዴሬሽንነት በኢትዮጵያ ውስጥ ሂደት እንዲፈርስ እና በኢትዮጵያ ውስጥ እንድትጠቃለል ያደረገው ሁኔታ በ1962 ዓ.ም ተፈጥሯል።

ከአውሮፓውያኑ ጋር ግንኙነት የነበራቸው አንዳንድ አካላት ጉዳዩን በመቃወም የወቅቱን መንግሥት መውጋት ጀምረዋል። ከተፈጠሩት ድርጅቶች መካከልም የኤርትራ ነፃነት ግንባር (ELF) እና የኤርትራ ሕዝብ ነጻነት ግንባር (EPLF) ይገኙበታል።

ይህ ሁኔታ ታዲያ ለ30 ዓመታት የወንድማማች መደማማትን ማስከተሉ አልቀረም። በዚህ መደማማት ታሪክ ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1991 የኤርትራ ሕዝብ ነጻነት ግንባር (EPLF) እና ሕወሓት የደርግን መንግሥት አስወግዶ አስመራን እና አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ቀደም ሲሉ የተሴሩ ሴራዎችን ለመተግበር ዕድል አግኝተዋል።

በ1984 ዓ.ም ከደርግ ውድቀት በኋላ ጊዜያዊ መንግሥቱን ለማቋቋም በተካሄደ ጉባኤ ላይ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ለታሪክ ተመዝግቦ በብላክ ላየን መጽሐፍ ላይ እንደሚገኘው የተደረገው ጉባኤ ጊዜያዊ መንግሥቱን ለማቋቋም እንጂ በኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን ሥልጣን እንደሌለው እና ሕጋዊ መንግሥት እስኪመሠረት ማንም የሚደርስበት ድምዳሜ አግባብ እንዳልኾነ መናገራቸው ተቀምጧል።

እ.ኤ.አ. በ1993 ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል የወቅቱ ገዥዎች ሲወስኑ ብዙ ታሪካዊ ስህተቶችም ተፈጽመዋል።

ከእነዚህ ስህተቶች መካክል የወደብ እና የባሕር በር ጉዳይ ይገኝበታል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ለአንድ ሚዲያ ሲናገሩ ኤርትራ ሀገር እንድትኾን ሲወሰን በባሕር በር ጉዳይ ላይ ሕወሓት ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል ነው የሚሉት።

እንደ አቶ ታምራት ገለጻ ከኾነ በወቅቱ በነበረው የጠረጴዛ ውይይት ላይ ነጮቹ ኤርትራ ሁለት ወደቦች ስላሏት ከኢትዮጵያ በ60 ኪሎሜትር ብቻ የሚርቀው የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያ እንዲኾን እንዲጠይቁ ለወቅቱ ፕሬዚዳንት በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጠይቀዋቸው አንፈልግም እንዳሉ አንስተዋል።

እነመለስ በወቅቱ የባሕር በር ጉዳይን ቀለል አድርገው እንዳዩት ነው አቶ ታምራት ያብራሩት።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ የራሷን ሉዓላዊት ሀገር ስትመሰርት ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታጣ በሀገር ውስጥ በግለሰቦች እና በፖለቲከኞች መካከል ከፍተኛ ክርክር ተደርጎ ነበር። ይህ ክርክር በዋናነት “የአሰብን ወደብ በተመለከተ” እና “ኤርትራ መገንጠል ነበረባት ወይስ አልነበረባትም” በሚሉ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።

በዚህ ክርክር ውስጥ በአንድ በኩል “አሰብ የኢትዮጵያ የሕይወት ደም ናት” የሚል አቋም የነበረው አካል ነበር። ይህ ቡድን ሀገሪቱ የባሕር በር ካጣች የውጭ ንግድ እንቅስቃሴዋ እና ኢኮኖሚዋ በእጅጉ እንደሚጎዳ ይከራከር ነበር። ስለዚህ አሰብ የግድ ከኢትዮጵያ ጋር መኾን አለባት የሚል ክርክር ያነሳል።

በተለይም በሕወሓት የሚመራው ሌላ ቡድን ደግሞ የአሰብን ወደብ በተመለከተ እና ኢትዮጵያ የኤርትራን መገንጠል ሙሉ በሙሉ መቀበል አለባት የሚል አቋም ነበረው። ይህ አቋም በጊዜያዊ መንግሥት ምሥረታ ላይ በተደረገ ጉባኤ እነመለስ ዜናዊ አንጸባርቀውታል።

ይህ ጉዳይ ታሪካዊ ስህተት መኾኑ እና በጠረጴዛ ዙሪያ የተደረገ ምክክር ላይ የታጣውን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ መልሶ ለማግኘት ሀሳቡን ማንሳት እና በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት ያስፈልጋል ይላሉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሉት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ምላሽ ማግኘቱ የግድ ይላል። ይህም በጠረጴዛ ዙሪያ መኾን አለበት ነው የሚሉት። የኢትዮጵያ ወዳጆች እና ወንድሞችም ለዚህ ውይይት መዘጋጀት አለባቸው ሲሉ በተደጋጋሚ በተፈጠሩ መድረኮች መልዕክታቸውን እያስተላለፉ ይገኛሉ። የባሕር በር ለኢትዮጵያ የሕልውና እና የብልጽግና ወሳኝ ጉዳይ ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ያሻዋል ግን ደግሞ በሰላማዊ መንገድ መኾን አለበት ነው የሚሉት።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲቲዩት ከፍተኛ ተመራማሪ አንተነህ ጌታቸው ( ዶ.ር) የቀይ ባሕርን ጉዳይ እና የኢትዮጵያን የባሕር በር ጉዳይ ማንሳት የሚያስፈራ አይደለም ይላሉ። ጉዳዩ ሲነሳ የግጭት እሳቤ ማንሳትም ተገቢ አይደለም ባይ ናቸው። ተመራማሪው ሲናገሩ በርግጥ ከነበረው ታሪክ እና ከቀጣናው ውስብስብነት አኳያ ጉዳዩ ቢያስፈራም አያሳስብም በውይይት የተፈጠረው ታሪካዊ ስህተት በውይይት ይፈታልም ይላሉ።

2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ እሳቤ በቀጣናው ላይ የተቀየረበት ዓመት ነው የሚሉት ተመራማሪው ይህም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ወደ ሥልጣን መምጣት ጋር የተገናኘ እንደኾነ ነው ያብራሩት።

የቀይ ባሕር ፎረም ቀደም ብሎ የተመሠረተ መኾኑን የሚናገሩት ተመራማሪው በተለይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ የፈጠሩት መቀራረብ ጥሩ ሁኔታ መፍጠሩ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የሦሥትዮሽ ስምምነት እንዲፈጥሩ እንዳደረጋቸው አስታውሰዋል። ይህ በተለይም የገልፍ ሀገራት እንዲሳቡ አድርጓልም ይላሉ።

በተለይ የተባበሩት አረብ ኤምሬት እና ሳዑዲ አረቢያ ጉዳዩ ስቦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሠሩት የማሠባሠብ ሚና የሸለሙበት ኹኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።

ይህ በኾነበት ተመሳሳይ ዓመት የቀይ ባሕር ፎረም ግብጽን ጨምሮ በሰባት ሀገራት በሳዑዲ አረቢያ እንደተመሠረተም አትተዋል። ይህም ኢትዮጵያን ባለማካተቱ ችግር ይፈጥራል ነው ያሉት። ይህም ኾን ተብሎ የተዘጋጀ ይመስላል ይላሉ።

ይኹን እንጂ ኢትዮጵያን ያገለለው ይህ ፎረም ዓላማውን እንዲያሳካ ኢትዮጵያ መካተት አለባት የሚል ሀሳብ ነው እየተነሳ ያለው ብለዋል።

ቀጣናው ሰላም እንዲኾን እና በኢኮኖሚም በሰላም እና ደኅንነትም ቀጣናው የተሻለ የሚኾነው የጋራ ተጠቃሚነት ሲኖር እንደኾነም ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያም በቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ ምክክር ለማድረግ እያደረገች ያለችው ጥረትም ለቀጣናው ሰላም ወሳኝ በመኾኑ ነው ብለዋል። በቀይ ባሕር ቀጣና ከፍተኛ ቁጥር ያለውን እና በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማግለል መሞከር የራሱ ጉዳት እንዳለው ማስረዳት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

ሀገሪቱ የቀይ ባሕር ተጠቃሚነቷን የምታረጋግጥበት ኹኔታም መፍጠር ያስፈልጋል ባይ ናቸው ተመራማሪው። የቀይ ባሕር ቀጣና ጉባኤን ኢትዮጵያ ማዘጋጀት እና ጉዳዩ በሰፊው የባሕሩ ተጋሪ እና የአካባቢው ሀገራት እንዲመክሩበት ማድረግ ለኢትዮጵያ ሀሳቧን ለመሸጥ እና ብዙ ሀገራት እንዲገዙት ማድረግ እንደሚያስችላት ነው የተናገሩት።

የቀይ ባሕር ቀጣና ሰላም የሚኾነው በቀጣናው ያለው ሰላም እና ከሽብርተኝነት እና ከባሕር ወንበዴዎች ለመከላከል ወሳኝ እንደኾነ እንደሚታመን ያስረዱት ተመራማሪው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ሰላም መኾን ጥቅሙ ለሁሉም እንደኾነ ለማስገንዘብ እና ሀገራቱ ኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ቀጣና አባል እንዲያደርጉ ሊሠራ እንደሚገባም ነው ያስረዱት።

ኢትዮጵያ የዚህ አባል መኾኗ ጥቅሙን ማሳየት ያስፈልጋልም ይላሉ። ኢትዮጵያ ቀስ እያለችም የቀይ ባሕር ተጠቃሚነቷ ወደ ነበረበት ታሪካዊ ምዕራፍ ለመመለስ በጠረጴዛ እንደሄደ ወደ ጠረጴዛው መጥቶ መታረም እንዲችል ማድረግ ይገባልም ባይ ናቸው።

ይህን ለማድረግ ግን በቅድሚያ ጉዳዩን እንደ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ ይህንንም ከመንግሥት እሳቤ አውጥቶ በሕዝብ ውስጥ የሚብላላ ሀሳብ ማድረግ ይጠይቃልም ይላሉ። ለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ኾኖ ጥቅሙን ያለ ልዩነት ማስከበር እንዳለበትም መክረዋል።

ጥቅሙን ሲያስከብር ግን በውይይት እና የምክክር መሥመር በመክፈት ሊኾን እንደሚገባ ነው ያመላከቱት። ጉዳዩ ሲነሳ የግጭት እሳቤ እንዳለው ከማሰብ በመውጣት የሰላማዊ ትግል እና የሰጥቶ መቀበል አካሄድ መኾኑን በደንብ ማጤን እና ቀጣናውን መረዳት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ እንዲኾንም ነው ያሳሰቡት።

ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ” የተሰኘው መጽሐፍ ተመረቀ።
Next article“የቱሪስት መስህቦች አንድነትን እና መከባበርን ሊፈጥሩ ይገባል” ሰላማዊት ካሳ