
አዲስ አበባ: መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት በተዘጋጀ መድረክ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃን አስመልክቶ”ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ” የተሰኘ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ተዘጋጅቶ ለምረቃ በቅቷል።
የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ ዓባይ ግዙፍ ውኃ ብቻ ሳይኾን የዘመናት ብሶት እና ቁጭት ምንጭ ነበር ብለዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ይህንን ቁጭት እንዲያበቃ ዓባይን በመገደብ አሳይተዋል ነው ያሉት። ለ84 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ዓባይ በኢትዮጵያውያን ትብብር እንዲገደብ የመገናኛ ብዙኃን ሚናውን ከመወጣት ባሻገር ይህንን መጽሐፍ ሰንዶ ለሕዝብ አቅርቧል ነው ያሉት። የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ዴኤታው ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው ዓባይ ለሌሎች ሲሳይ ለኛ መሳቀቂያ ኾኖ ለዘመናት ቢቆይም በዚህ ትውልድ ተጀምሮ ተጠናቋል ሲሉ ገልጸዋል።
ከማንኛውም ሴራ እና ኃይል ጠብቀን በቁጭት እና በትጋት ለምርቃቱ በማብቃታችን ልንኮራ ይገባልም ብለዋል አቶ ተስፋሁን። የዚህ መጽሐፍ ዐብይ ዓላማም እንደነ ላሊበላ፣ አክሱም እና ሌሎችም እንዴት ተገነቡ ብሎ ከመጠየቅ ባሻገር የራስን አሻራ ለማሳረፍ መነሳሳትን ለመፍጠር የሚያስችል ተምሳሌትነትን በታላቁ ዓባይ ሕዳሴ ግድብ ለመገንባት የተሄደውን ርቀት እና ብርሃንነቱን” ብርሃን ፈንጣቂው ዓባይ” በሚል ሰንዶ ማሳየቱ ነው ብለዋል። ሁሉም የየራሱን አስተዋጽኦ በማበርከቱ ይህንን የመሰለ ታላቅ ፕሮጀክት ዕውን ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። ይህም ተባብረን በጋራ ከቆምን ማሳካት የማንችለው ምንም ነገር እንደሌለ ማሳያ መኾኑን ገልጸዋል ።
መጽሐፉ በ252 ገጾች እና በሦስት ክፍሎች ከመግቢያው ውጭ በ17 ርዕሶች ተቀንብቦ የቀረበ ነው። ከያዛቸው ርእሶች መካከልም የዘመናት ቁጭት፣ የዓባይ ወንዝ መልክዓ ምድራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ፍርደ ገምድል ስምምነቶች፣ ዓባይ ቤቱ አደረ፣ ሴራን የመከተ ተግባራዊ አንድነት፣ ስለ ዓባይ የተጋመዱ ክንዶች፣ ኢትዮጵያን ከዓባይ የማግለል ታሪካዊ ሴራዎች እና ዲፕሎማሲያዊ ትግሎች፣ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና መገናኛ ብዙኃን፣ ማን ምን አለ?፣ የግድቡ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች፣ ጀምሮ መጨረስን ያስተማረ እና የድል ሰንደቅ የሚሉ ከንጉሱ ጊዜ የተጀመረውን ጥንስስ እስከ ፍጻሜው የታለፈውን መንገድ የሚዘክሩ ጉዳዮች ተነስተውበታል። በዕለቱ በመጽሐፉ ላይ የተመሠረተ ውይይትም ተካሂዷል።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!