
ባሕር ዳር: መስከረም 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ጥንታዊ እድገቷ እና ውጫዊ ግንኙነቷ መሠረቱ ውኃ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡
ምሥራቅ አፍሪካዊቷ” የውኃ ማማ” ኢትዮጵያ ሥልጣኔዋ፣ ዝማኔዋ፣ ዲፕሎማሴዋ፣ ጥበቧ እና ማንነቷ ከውኃ ጋር የተንሰላሰለ ነው፡፡ የቀይ ባሕር እና የባሕረ ሰላጤው አካባቢ ለኢትዮጵያ ጥንታዊ የባሕር ላይ ጉዞ መልህቅ ነበሩ፡፡ በአክሱም ሥልጣኔ የተራቀቀችው ኢትዮጵያ በገናናዋ ግሪክ፣ በጥንታዊቷ ፋርስ፣ በጠንካሮቹ ሩቅ ምሥራቅ እና በጠቢባኑ መካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ድረስ የውጭ ንግድን በማመቻቸት ስሟ ገናና እንደነበር ይነሳል፡፡ በመካከለኛው ዘመንም ኢትዮጵያ እንደ ዘይላ እና በርበራ ካሉ ዝነኛ የወደብ መዳረሻዎች ጋር ስሟ አብሮ ይነሳል፡፡
ገናና የነበረው የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ታሪክ እጥፋት የገጠመው ግን አሁን በቅርቡ ነበር፡፡ ባሕር ኃይሏ ተበትኖ፣ መውጫ መግቢያዋ ተከድኖ “ላንድ ሎክድ” ከተባለች ከጎልማሳነት የዘለለ ዕድሜ አላስቆጠረችም፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት ሀገር ዓለም አቀፋዊ የንግድ መስመሮችን በነጻነት ማግኘት አለመቻሏ የፈጠረው ተጽዕኖ እንደተጠበቀ ኾኖ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የባሕር በር ጥያቄን አጀንዳ አድርጎ ማንሳትም ኾነ መሞገት ነውር ኾኖ የቆየበት መንገድ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ሂደት ውስጥ የላቀ መረዳት እንዳላቸው የሚነገርላቸው እውቁ ዲፕሎማት ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሌ እንደሚሉት በዘመናዊው የዓለም አቀፍ ሕግ ውስጥ ካሉት ፈታኝ ሁኔታዎች አንዱ ወደብ ለሌላቸው ሀገሮች የባሕር በር መዳረሻን ማረጋገጥ ነው ይላሉ።
ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ኖሯቸው ወደብ አልባ ከኾኑ የዓለም ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሀገር ናት፡፡ ከቀይ ባሕር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ የባሕር በር አልባ ኾና ቆይታለች።
በታሪክ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ሃብት እና ንብረት የነበረው የአሰብ ወደብ አንድ ወቅት በገጠማት ፖለቲካዊ ስብራት ምክንያት ከእጇ እንዲወጣ መደረጉ ለበርካቶች “የእግር እሳት” ኾኖ ቆይቷል፡፡ ምጣኔ ሃብታዊ ጥገኝነት፣ ኢ ፍትሓዊ ተጠቃሚነት፣ ደኅንነት እና የሉዓላዊነት ጥያቄዎች ከባሕር በር ጥያቄ ጋር በእጅጉ እንደሚቆራኙም ፕሮፌሰር ብሩክ ያነሳሉ፡፡ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ከ1990ዎቹ መባቻ ጀምሮ የባሕር በር አልባ ለሆነችው ኢትዮጵያ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሳይቀር ተሟግቷል ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሌ። የወደብ ጥያቄው ተዳፍኖ እንዲቀር ምክንያቱ በጊዜው ሀገሪቷን ይመራ የነበረው መንግሥት ብቻ ነበር ይላሉ፡፡ አሁን ላይ የባሕር በር ጉዳይ አጀንዳ መኾኑ ትውልዱን ወደ ቀደመ ታሪኩ የሚመልስ እንደሚኾንም አንስተዋል፡፡
በፖለቲካዊ ስህተት እና በውጭ ኃይሎች ፍላጎት ከቀይ ባሕር አካባቢ ገለል ተደርጋ የቆየችው ኢትዮጵያ ለምጣኔ ሃብታዊ ቁዘማዋ እና ጂኦ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቷ ትልቅ ምክንያት ኾኖባት ቆይቷል። ያኔ የባሕር በር ጥያቄን የሚያነሱ ሁሉ የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚዎች፣ ግጭት ቀስቃሾች፣ የቀደመ ሥርዓት ናፋቂዎች እና ሌሎች ስያሜዎች ይሰጧቸው ስለነበር በባሕር በር ጉዳይ የራስን ሃብት እና መብት መጠየቅ የሚያሸማቅቅ ኾኖ ቆይቷል፡፡
ኢትዮጵያን ከባሕር በር ጋር ለማገናኘት የሚደረገው እንቅስቃሴ አሁናዊውን ሳይኾን መጻዒዋን ኢትዮጵያ ታሳቢ ያደረገ ነው ይሉታል፡፡
በ2025 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 150 ሚሊዮን ገደማ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡ የሀገሪቷ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴም እያደገ መጥቷል፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን ኢትዮጵያ የሕዝብ ብዛቷ የሚፈልገውን እና የምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዋ የሚሸከመውን የባሕር በር ፍላጎት ማሟላት የሕልውና ጉዳይ መኾኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ በአፍሪካ ጉዳዮች ኤክስፐርት የኾነው ጋዜጠኛ ግሬጎሪ ኮፕሌይ የግብጽ ዋና አላማዋ ኢትዮጵያ በቀጣናው የበላይነት እንዳይኖራት በባሕሩ ዙሪያ ማግለል ነው ይላል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስቀምጥ “ወደብ አልባ ኾኖ ታላቅ የኾነ ሀገር የለም” ነው የሚለው።
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!