የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል።

4
አዲስ አበባ: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መድኃኒት እና ሕክምና መገልገያዎች አምራች ዘርፍ ማኅበር 22ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ተካሂዷል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በመድኃኒት እና ሕክምና መገልገያዎች አምራች ዘርፍ ለመሠማራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ረገድ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል። በዚህም ለጤናው ዘርፉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል ነው ያሉት። በዘርፉ በተኪ ምርቶች ላይ ለሚሠማሩ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አክሞ ማዳን ላይ መሠረት ያደረገውን የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሕክምና ግብዓት አቅርቦት ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ነው ያሉት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ደረጀ ድጉማ (ዶ.ር) ናቸው። ማኅበሩ ጥራት እና እሴት የተጨመረባቸውን የሕክምና መገልገያዎች የማምረቱ ሂደት ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት እና ሕክምና መገልገያዎች አምራች ዘርፍ ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳንኤል ዋቅቶሌ (ዶ.ር) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመድኃኒት እና የመገልገያ ግብዓቶችን በሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ይነሱ የነበሩ ተግዳሮቶችን ከመቀነስ አንጻር ጉልህ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል። ከውጭ ይገቡ የነበሩ የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያዎች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት። በጉባኤው ላይ መድኃኒቶችን እና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችሉ እና በአግባቡ ለተጠቃሚዎች የሚደርሱበትን ሂደቶች በሚመለከት ውይይት ተደርጓል።
ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleምክር ቤቶች ሕዝብ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲኾን መሥራት ይገባቸዋል።
Next articleምክር ቤቶች የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዋነኛ ዓላማቸው ነው።