
ባሕር ዳር: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በሲዳማ ክልል ሕዝባዊ የድጋፍ እና የደስታ መግለጫ ሰልፍ ተካሂዷል።
የድጋፍ ሰልፉን አስመልክተው መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በፊቼ ጨምበላላ የዘመን ቆጠራ ዕውቀት እና ፍልስፍናው የሚታወቀው የሲዳማ ሕዝብ የሕዳሴን መጠናቀቅ ውብ በሆነው የቄጣላ ሥርዓቱ ደምቆ በአደባባይ አክብሯል ብለዋል።
ሕዳሴ የዓባይን ወንዝ እራት እና መብራት ሆኖ የኢትዮጵያ ልጆችን የልማት ተስፋ እውን ሊያደርግ እንደ አድማስ ዐለት በጽናት እና በትብብር መንፈስ የቆመ የሕዝቦች እውነት እና ታሪክ መኾኑን ገልጸዋል።
ዓባይን ከብዙ ዓመታት በኋላ ከሀገሩ ጋር ያስማማው የሕዳሴ ድል የሲዳማ ክልልንም የሀገራዊ የልማት እቅዶች በይቻላል መንፈስ እንዲሠራ ዕድል ይፈጥርለታል ነው ያሉት።
ሕዳሴ በሀገር ወዝ ተሞሽሮ ጉባ ላይ የቆመ የልማት ሐውልታችን እና መቻላችን የተረጋገጠበት ሕዝባዊ ዐሻራ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!