ያሆዴ የሀዲያ የዘመን መለወጫ በዓል በሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ነው።

3
አዲስ አበባ: መስከረም 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ያሆዴ” የሀዲያ የዘመን መለወጫ በዓል ያለልዩነት በልዩ ድምቀት እና በአንድነት ከሚከበሩ ቱባ በዓላት አንዱ እና ቀዳሚው ነው። ያሆዴ የሀዲያ ሕዝብ አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ዓመት የሚቀበልበት ልዩ በዓሉ ነው።
የያሆዴ በዓል ሀዲያ ዘመኑን የሚቆጥርበት ትልቅ በዓል ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ከአዲስ ተስፋ፣ ከልምላሜ፣ ለሀገር ሰላም ጸሎት ከማድረግ፣ ከብርሃን ጋር የሚገናኝ ተደርጎም ይወሰዳል። በዓሉም የክረምቱ ጭጋግ፣ ወንዝ መሙላት አልፎ በጸደይ መባቻ የሚከበር እንደመኾኑ መጠን ብሩህ ተስፋ የሰነቀ፣ የብርሃን ጮራ ያዘለ የመልካም ምኞት ማሳያ በዓል መኾኑን የብሔረሰቡ አባቶች ይናገራሉ።
በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞም ሁሉም ሰው የራሱን ድርሻ ለመወጣት ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል፤ ከዚያ በኃላ ሁሉም በጋራ በደስታ በዓሉን ያከብራል፤ ፈጣሪውንም ያመሰግናል ነው ያሉት። የያሆዴ በዓል ሲነሳ ሁሌም አብሮ የሚነሳው የያሆዴ ጭፈራ (ጨዋታ) ነው።
ጭፈራውን ወጣት ወንዶች በአካባቢያቸው ተሠብሥበው በየቤቱ እየተዘዋወሩ ምሽቱን ሙሉ የሚጨፍሩበት ባሕላዊ ጨዋታ ነው። በዚህ ዕለት ማታ ፉኒታ ( ሆያ ሆየ) የሚጨፈርበት እና ጨፋሪዎች ደግሞ “ከዚህ ቤት ችግር ይውጣ፣ በሽታ ይውጣ” ብለው ችቦ እያቀጣጠሉ ይጨፍራሉ።
ጨፋሪዎች መርቀው ሲወጡ የቤቱ አባወራ እና እማወራ ደግሞ እናንተም እደጉ በማለት ይመርቁ እና ይሸኟቸዋል። ይህ ዕለት ሁሉም የሀዲያ ሕዝብ የሚመራረቅበት ነው። ያሆዴ ጭፈራን ከሌሎች ጭፈራዎች የተለየ የሚያደርገው ልጆች ወላጆቻቸውን የሚመርቁበት በመኾኑ ነው።
በየገቡበት ቤት ሁሉ አተካና እና ለበዓሉ ተብሎ የተዘጋጁ ምግቦችን እየበሉ የቤቱን አባወራ እና እማወራ ይመርቃሉ። ለዚህ በዓል ሴቶችም ከአለባበስ እስከ ፀጉር አሠራር ድረስ በተስተካከለ ሁኔታ ይዘጋጃሉ።
የሀገር ሽማግሌዎች ተሰልፈው ሥርዓቱን ያስጀምራሉ፤ ይከታተላሉ፤ ይመርቃሉ። በዚህ በዓል ሴቶች ቀደም ብለው ሥራቸውን ይጀምራሉ። ቤታቸውን ያዘጋጃሉ፤ በኅብረትም ሥራ ይሠራሉ።
ወንዶች ደግሞ እንጨት ያዘጋጃሉ። ሰንጋ ይገዛሉ። ሕጻናት ጦምቦራ (ችቦ) ቀድመው ይሠራሉ። በያሆዴ ሰው ብቻ ሳይኾን ከብቶችም አዲስ ዓመት የሚቀይሩበት በመኾኑ ጥብቅ ወይም ክልክል ሳር ይፈቀድላቸዋል። በዓሉ ከመከበሩ በፊት በርካታ ዝግጅቶች ይካሄዳሉ። እነዚህም ክንውኖች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ እንደኾነም ይነገራል።
ያ ሆዴ የተጣላ ታርቆ፣ ያለው ለሌለው አካፍሎ በመተሳሰብ እና በፍቅር መጭውን አዲስ ዓመት በደስታ የሚቀበልበት ልዩ የሀዲያ ሕዝብ መገለጫ በመኾኑ አስታራቂዎችም ቂም ይዞ አዲስ ዓመትን መቀበል አይቻልም በማለት የተጣሉ ሰዎችን ያስታርቃሉ። በሀዲያ አዲስ ዓመትን ያ ሆዴን ለመቀበል በቅድሚያ አንድ ሰው ከተጣላው ጋር እርቀ ሰላም ማውረድ አለበት። ቂም ይዞ አዲሱን ዓመት መቀበልም ኾነ ማንኛውንም አይነት ዝግጅት ማድረግ አይችልም።
በርካታ የሀገር ሽማግሌዎችም እየዞሩ የተጣላን ያስታርቃሉ። ታዲያ የተጣሉ ሕጻናትም ቢኾኑ ተፈላልገው ይታረቃሉ። ወይንም አስታርቁኝ ብለው እኩዮቻቸውን ይልካሉ። ይህም ሁኔታ በማኅበረሰቡ ዘንድ መረጋጋት እንዲኖር ከማድረጉ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ከዚህ በዓል ማግስት ጀምሮ የሀዲያ ሕዝብ የመረዳዳት ባሕሉን በስፋት የሚያንፀባርቅበት፣ ጥልን እና ቂምን በማስወገድ በአዲስ መንፈስ በማኅበረሰቡ መካከል ግንኙነትን በማጠናከር እና ማኅበረሰብን እንዴት መለወጥ እንዳለባቸው የሚመካከሩበት ብሎም አቅጣጫ የሚይዙበት በመኾኑ ጥቅሙ የጎላ ነው። እንዲሁም በልማት፣ በግብርና፣ በንግድ እና በሌሎች ሥራዎች ላይ የሚመክሩበት በዓል ነው።
ለሥራው ባለው ትጋት እንደምሳሌነት የሚጠቀሰው የሀዲያ ሕዝብ ለሥራ ከተሰማራባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ከሀገር ውጭም ሳይቀር ያሆዴ በዓልን ከቤተሰብ፣ ከዘመድ አዝማድ፣ ከአብሮ አደግ እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር አብሮ ለማክበር ወደ ሀዲያ ይተማል። ይህ በዓል ዛሬ በሆሳዕና ከተማ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ሲኾን የተለያዩ ጎረቤት እና ወንድም እህት ብሔሮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እና የሰንጋ ስጦታዎችን ይዘው ተገኝተው በጋራ በዓሉን እያከበሩ ይገኛሉ።
በበዓሉ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ.ር)፣ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)፣ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ እና ሌሎች የፌዴራል፣ የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀደም ሲል የነበረውን የተሳሳተ ትርክት የቀየረ ነው፡፡
Next article“የሲዳማ ሕዝብ የሕዳሴን መጠናቀቅ ውብ በሆነው የቄጣላ ሥርዓቱ ደምቆ በአደባባይ አክብሯል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ