
አዲስ አበባ: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓልን ለማክበር የተደረጉ መንፈሳዊ ዝግጅቶችን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መግለጫ ሰጥታለች።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሚከበሩት የአደባባይ በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ በዓል አንዱ እና ዋናው መኾኑን መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የሸገር ከተማ አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ ገልጸዋል።
ብጹዕነታቸው ቤተክርስቲያኗ የመዳን ምስጢር የኾነው “በዓለ መስቀሉ ሲከበር ምዕመናኑ በመስቀሉ የተደረገልንን በማሰብ ሊኾን ይገባል” ብለዋል። መስቀል የሰላም በዓል እንደመኾኑ በዓሉን በሥርዓተ ኦርቶዶክሳዊ ማንነት በአለባበስ እና በዝማሬ ሰላምን በመስበክ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
በዓሉ ዓለም ዓቀፋዊ እውቅና ያለው እንደመኾኑም መስቀልን ለማክበር ስንሰባሰብ የሚተላለፉ መልዕክቶች ፍቅርን እንጂ ጥላቻን እንዳይሰበኩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።
በዓሉን በተሟላ መንፈሳዊ ሥርዓት ለማክበር የረጅም ጊዜ ዝግጅት መደረጉን በመግለጽም በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ክብረ መስቀሉ ለዓለም የሚታወጅበት፣ የቤተክርስቲያኗ ትውፊት እና ሥርዓት በይፋ የሚገለጥበት በመኾኑ ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው ለሁከት የሚንቀሳቀሱ አካላት ተቀባይነት የላቸውም ነው ያሉት።
ለ2018 ዓ.ም የመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ቤተልሔም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!