የዓለም የቱሪዝም ቀንን ማክበር የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት ያስችላል።

8

አዲስ አበባ: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ቱሪዝም ለዘላቂ ለውጥ” በሚል መሪ መልዕክት በዓለም ለ46ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ38ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው የዓለም የቱሪዝም ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ መርሐ ግብሮች መከበሩን ቀጥሏል።

የዓለም የቱሪም ቀንን አስመልክቶ መስከረም ዘጠኝ የጀመረው የቱሪዝም ሳምንት በሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ “የያሆዴ” በዓል ዋዜማ በክልሉ ርእሰ ከተማ ሆሳዕና ላይ አውደ ጥናት መካሄድ ጀምሯል ።

በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሆሳዕና ከተማ ከንቲባ ሳሙኤል ሽጉጤ ከተማዋ ለኑሮ፣ ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትኾን የዋና እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በኮሪደር ልማት እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር የሥራ አመራር ዋና ሥራ አሥፈጻሚ
ግርማ መላኩ ሚኒስቴሩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ከልል በዓሉ እንዲከበር ያደረገበት መንገድ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት መኾኑን ገልጸዋል።

ከዓለም የቱሪዝም ቀን መሪ መልዕክት ጭብጥ ጋር በማስተሳሰር የተለያዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ዘርፉ ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለውን ፈርጀ ብዙ ፋይዳ ለመላው ሕዝባችን ለማስገንዘብ ነው ብለዋል።

ይህ መኾኑ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲጎለብት እና ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ የጉብኝት መስመሮች መነሳሳትን ለመፍጠር ያስችላል ነው ያሉት።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ሳሙኤል መንገሻ በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበርበት ክልል መኾኑ ፋይዳው ትልቅ ነው ብለዋል።

ክልሉ በብዝኃ ማንነት የታደለ፣ ዘመናዊ የቱሪዝም ጽንሰ ሃሳብ ከመጀመሩ በፊትም እንግዳ ተቀባይ፣ ታታሪ እና ሀገር ወዳድ፣ ማንነቱን እና ባሕሉን አክባሪ ሕዝብ የሚኖርበት መኾኑን አንስተዋል። ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ መስህቦች ያሉበት፤ ለመንቀሳቀስ ምቹ የኾነ ሰላማዊ ክልል መኾኑን ነው የተናገሩት።

የሚደረጉ ውይይቶች እና ሁነቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ግንዛቤ እና አቋም ለመያዝ ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

ሀገራዊ የቱሪዝም አቅምን ለማጎልበት ክልሉ
54 የቱሪዝም መስህቦችን በመለየት እና 13ቱን በቅድሚያ ለይቶ በመጀመሪያ ዙር ለማልማት የዲዛይን ሥራ ተሠርቶ ወደ ተግባር ተገብቷል ነው ያሉት።

ለአገልግሎት አሰጣጥ ለዘርፉ ምቹ መኾን የሚያግዙ 21 አዳዲስ ሆቴሎች በተለያዩ የክልሉ ማዕከላት ተመርቀው ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

እንደ ክልል የቱሪዘም ፍሰቱ በ14 ነጥብ 5 በመቶ እያደገ መምጣቱን ያነሱት ኀላፊው ባለፈው ዓመት ብቻ ከ546 ሺህ የሀገር ውስጥ እና ከ21 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ መዘዋወር ችሏል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመስቀል በዓል ሥርዓቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር ሀሉም የድርሻውን እንዲወጣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ጠየቁ። 
Next articleኅብረተሰቡን የመንገድ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።