
አዲስ አበባ፡ መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በ2018 የመስቀል በዓል አከባበር ዙሪያ እየተወያዩ ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀድያ፣ ስልጤ እና አዲስ አበባ አሕጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ ሕርያቆስ የሰው ልጆች ነፃ የወጡት በመስቀል ላይ በመሆኑ ነጻ የወጣንበትን እና የዳንበትን መስቀል ማክበር ተገቢ ነው ብለዋል።
በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል። በበዓሉ ላይ ኮሽታ እንኳን ቢከሰት በትዕግስት በመፍታት ምዕምናን በሰላም አንዲያከብሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ሊዲያ ግርማ የመስቀል በዓል በዩኒስኮ የተመዘገበ የዓለም ሃብት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል ባሕሎች እና ጥንተ ሃይማኖቶች ተከባብረው የሚኖሩባት ለመሆኗ መስቀል አንዱ ማሳያ መኾኑን አንስተዋል።
በዓላትን ተጠቅመው ችግር ለመፍጠር የሚታትሩ እንዳሉ በዳሰሳ እያየን ነው ያሉት ኀላፊዋ ይህንን በመከላከል ለሀገራችን ለሚጠቅመው ሰላም መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል። ሰላም የእኛን አንድነት ይጠይቃል ነው ያሉት።
በዓሉ ሥነ ሥርዓቱን ጠብቆ እና በፍጹም ሰላም እንዲከበር ማድረግ አለብን ብለዋል።
የዛሬው መድረክም ስለበዓሉ አከባበር የመጨረሻ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መኾኑ ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!