
ባሕር ዳር: መስከረም 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ታይሮይድ በአንገት ስር የሚገኝ እና ለሰውነታችን ወሳኝ የኾኑ ሆርሞኖችን የሚያመርት አካል ነው። እነዚህ ሆርሞኖች የምግብ መፈጨት፣ የሰውነት ሙቀት፣ ስሜት እና ሌሎች በርካታ ተግባራትን ይቆጣጠራሉ። የእንቅርት በሽታ የሚባለው ይህ ታይሮይድ የሚያመነጨው ሆርሞን ሲቀንስ ወይም ሲጨምር የሚፈጠር የጤና ችግር ነው።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው ወጣት ሰለሞን ሲሳይ የእንቅርት በሽታ ታሞ እንደነበር ከአሚኮ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል። ወጣቱ ስለ ሕመሙ ሲናገር ብዙ እንደተሰቃየ ነው የተናገረው። የዚህ በሽታ ምልክት አዲሴ ስለነበር እና ያላሰብኩት ስለኾነ በወቅቱ የምተርፍ አልመሰለኝም ነበር ነው ያለው። ዐይኖቹ መፍጠጥ፣ የሰውነት መክሳት፣ የምግብ ፍላጎት መጨመር፣ ፀሐይን መቋቋም አለመቻል፣ ቶሎ ቶሎ ውኃ መጥማት፣ የጸጉር መሳሳት እና መነቃቀል፣ ሰዎችን መጥላት፣ ጭንቀት እና መሰል ምልክቶች ይታዩበት እንደነበርም ነው የነገረን።
ወጣቱ ወደ ሕክምና ተቋም ሲሄድ የእንቅርት በሽታ መኾኑ እንደተነገረውም ገልጿል። ወዲያው መድኃኒት እንዲጀምር እና ቀዶ ጥገና እንዲሠራለት ተደርጎ ጤናው መመለሱንም ገልጿል። በተክለ ሃይማኖት ጠቅላላ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር ምንተስኖት ድረስ ይህ በሽታ በአንገት ላይ እብጠት በመፍጠር የሚታወቅ ነው፤ በአብዛኛው ከአዮዲን እጥረት ጋር የሚያያዝ በሽታ ነው ብለዋል። የእንቅርት በሽታ እንዲከሰት የሚያደርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች ብለው ከጠቀሷቸው ውስጥ በተራራማ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜ መኖር የአዮዲን እጥረት እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል ነው ያሉት። ከአዮዲን እጥረት ውጭ ያሉ አንዳንድ የእንቅርት በሽታዎች ደግሞ ከዘር ጋር ሊያያዙ እንደሚችሉም አስረድተዋል። በሽታው ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ በብዛት ይከሰታል ብለዋል።ምንም እንኳን በሽታው በየትኛውም የዕድሜ ሁኔታ ቢከሰትም ከ30 እስከ 60 ዓመት ባሉ ሰዎች ላይ ይበልጥ ይስተዋላል ነው ያሉት።
እንደ ጠቅላላ ሐኪሙ ገለጻ የበሽታው ምልክቶች እንደ የታይሮይድ ሆርሞን መጠን መጨመር ወይም መቀነስ ሊለያዩ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።

ከፍተኛ የኾነ የረሃብ ስሜት እና የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የባሕሪ ለውጥ፣ መበሳጨት እና ጭንቀት፣ የዐይን ማልቀስ እና እብጠቱ ወደ ውጭ መውጣት፣ ላብ እና የሙቀት ስሜት፣ የልብ ምት ፍጥነት መጨመር፣ ከመጠን ያለፈ ድካም፣ የፀጉር መነቃቀል የታይሮይድ ሆርሞን መጠን ሲጨምር የሚታዩ ምልክቶች እንደኾኑም ዶክተሩ ጠቅሰዋል።

የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና የሰውነት ውፍረት፣ ከፍተኛ እንቅልፍ፣ ትኩረት ማጣት እና ድካም፣ የሆድ ድርቀት፣ ብርድ ብርድ ማለት ተጠቃሽ ምልክቶች እንደኾኑ ዶክተር ምንተስኖት አብራርተዋል።

የእንቅርት በሽታ ሲከሰት አንገት አካባቢ እብጠት (ጉብታ) መኖር፣ ለመዋጥ መቸገር፣ የትንፋሽ ማጠር እና የድምጽ መለዋወጥ እንደሚኖርም ሐኪሙ ተናግረዋል።

የእንቅርት በሽታን ለመለየት እና ለማከም የሚረዱ የተለያዩ መንገዶች አሉ ያሉት ዶክተር ምንተስኖት ከነዚያም ውስጥ የሆርሞን ምርመራ አንዱ እንደኾነ አስረድተዋል። በደም ውስጥ የሚገኘውን የቲ ኤስ ኤች፣ ቲ ስሪ እና ቲ ፎር ሆርሞኖች መጠን ለማወቅ የሆርሞን ምርመራ ይደረጋል ነው ያሉት ።
ሌላው የአንገት አልትራሳውንድ ሲኾን የእብጠቱ መንስኤ ታይሮይድ መኾኑን ለማረጋገጥ የሚደረግ ምርመራ እንደኾነም ነው የጠቆሙት።
ኤፍ ኤን ኤ ሲ እብጠቱ አጠራጣሪ በሚኾንበት ጊዜ ካንሰር መኾኑን ለማጣራት ከእብጠቱ ላይ ትንሽ ናሙና በመርፌ ተወስዶ የሚደረግ ምርመራ እንደኾነም ዶክተር ምንተስኖት ተናግረዋል።
ኢሲጂ እና ኢኮካርዲዮግራፊ ሌላው የምርመራ አይነት ነው። ሆርሞን በመብዛቱ ምክንያት በልብ ላይ የደረሰን ጉዳት ለመፈተሽ የሚረዳ ነው ብለዋል።

የእንቅርት በሽታ ሕክምና እንደየ ምክንያቱ ይለያያል ይላሉ ዶክተር ምንተስኖት።
የሆርሞን መጠን ሲጨምር ወይም ሲቀንስ ለመቆጣጠር መድኃኒቶች ይታዘዛሉ የሚሉት ሐኪሙ የልብ ምትን ለማስተካከልም የሚያግዙ መድኃኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ ብለዋል።
የእብጠቱ መጠን ትልቅ ከኾነ እና በቁጥጥር ስር ለማዋል ካልተቻለ ወይም ካንሰር የመኾን ጥርጣሬ ካለ ቀዶ ሕክምና ዋነኛ መፍትሔ ሊኾን ይችላል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሐ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!