
ባሕር ዳር፡ መስከረም 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያውያን የሀገር ፍቅር እና አቅም ተገንብቶ ለፍጻሜ የበቃው ግዙፍ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ለፍጻሜ መብቃቱን ተከትሎ በደሴ ከተማ “በኅብረት ችለናል” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልዓከ ሰላም ፈንታ አበራ ዓባይ ብርሃን፣ ልማት፣ አሳ፣ ፍራፍሬ ኾኖ በሚያበላበት በዚህ ዘመን ስላደረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለመገደብ የጣሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት እንደነበሩም ተናግረዋል። እናንተ የምትሰሙትን ሊሰሙ፣ የምታዩትን ሊያዩ የወደዱ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነገር ግን አላዩም፤ አልሰሙም፤ ሞት ቀድሟቸዋል፤ እናንተ ግን ጀሮዎቻችሁ እየሰሙ እና ዐይኖቻችሁ እያዩ ዛሬ ደርሳቹሀልና እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን ነው ያሉት።
መጽሐፍ ቅዱስ ጊዮን በማለት የዓባይ ወንዝን እንደሚጠራውም ገልጸዋል። ዓባይ በገነት መካከል ካለች እጸሕይወት ከምትባል ዛፍ ስር ፈልቆ ወደ ኢትዮጵያ ፈሶ እና ዙሪያዋን ከቦ፣ ባርኮ እና ቀድሶ ካስደሰተ በኋላ ወደ ግብጽ በመሄድ ለግብጻውያን ሕይወት ኾኖ እያስደሰተ የሚገኝ መኾኑን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ዓባይ ኢትዮጵያ ላይ ወንበዴ እና ጉልበታም ነበር፤ የኢትዮጵያን አፈር እና ማዕድን ቀምቶ ለባዕድ ሀገር የሚሰጥ ነበር ነው ያሉት።
አሁን ግን ከእሱ የበለጠ ጉልበታም ገጥሞት ተገድቧል ነው ያሉት። ዓባይ እንዳይሮጥ፣ እንዲረጋጋ፣ ወደ ሰው ሀገር እንዳይሄድ፣ ከዚሁ ሀገሩን እንዲያስደስት ኾኗልና እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን ብለዋል።
“ሩህሩህ ነሽ እና ኢትዮጵያ ሀገሬ”
ክብርና ምስጋና ለአንች ይሁን ዛሬ” ብለውም በስንኝ ደስታቸውን አጋርተዋል።
ሌላኛው መልዕክት ያስተላለፉት የደሴ ከተማ ዑለማ ምክር ቤት ፈትዋ ዘርፍ ኀላፊ እና የአረብ ገንዳ መስጅድ ምክትል ኢማም ሼህ ኡመር አሊ በሀገር ውስጥም ኾነ ከሀገር ውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ለዛሬው ቀን አደረሳችሁ ብለዋል።
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ‘አራት ወንዞች በምድር ላይ አሉ፤ ሁለቱ ከስር ሁለቱ ከላይ ይፈልቃሉ፤ ከታች ያሉት የጀነት ምንጮች ናቸው ፤ ዓባይም ከጀነት የሚፈልቅ ውኃ ነው ይላሉ፤ ስለዚህ ሀገሬ ኢትዮጵያ የጀነት ውኃ መፍለቂያ ናትና ደስ ይለኛል፤ ፈጣሪ ይመስገን ነው ያሉት።
ዓባይ ሲሸሸን፣ ሲኮበልልብን፣ የጀነት ውኃን ሳንጠቀም ኑረን፤ በበሳል፣ በጀግና እና በአስተዋይ መሪዎቻችን በራሳችን፣ ለራሳችን ገድበን ለፍጻሜ አብቅተነዋልና ደስ ብሎናል ብለዋል።
ከእነ ነጃሽ እና ከእነ ቢላል ጀምሮ ይች ሀገር ትልልቅ ሰዎች ያሉባት፤ የበረካ ሀገር ናትም ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የገለጿቸው
አዳዲስ ፕሮጀክቶችንም የዓባይ ግድብን እንዳሳካን እናሳካቸዋለን ያሉት ሼህ ኡመር አሊ ሁሉም ሰው ግን ሰላም፣ የአላህን ዕዝነት እና በረከት ይፈልጋልና አላህ ሀገራችን የሰላም፣ የዕዝነት እና የበረከት ሀገር ያድርጋት ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!