
ባሕር ዳር፡ መስከረም 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ ዛሬ በመላው የአማራ ክልል ሕዝቡ ከመሪዎቹ ጋር ወደአደባባይ በመውጣት የደስታ እና የምስጋና ሰልፍ ሲያካሂድ ውሏል።
የአማራ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽንም የግድቡን መመረቅ ተከትሎ የተፈጠረውን ደስታ ከመላው የክልሉ ሕዝብ ጋር በመኾን መካፈሉን ገልጿል።
ፌዴሬሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባሰፈረው መግለጫ እንዳለው በአፍሪካ ትልቁ የሕዳሴ ግድባችን የኢትዮጵያ አንድነት፣ ፅናት እና ቆራጥነት መገለጫ ነው።
የሕዳሴው ግድብ ትውልድን በሀገራዊ መተሳሰብ፣ በደስታ እና በኩራት ያነሳሳ፣ የትውልድ ራዕይም በዕውን የተገለጠበት ፕሮጀክት ስለመኾኑም መግለጫው ጠቁሟል። ባሕር ዳርን ጨምሮ በመላው የክልሉ ከተሞች ወጣቶች ከሕዝቡ ጋር ወደ ዓደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ስለመካፈላቸውም ተነስቷል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የንጹህ እና ዘላቂ ኃይል ምንጭ ብቻ ሳንኾን የኢትዮጵያ ሕዝቦች የከፈሉትን መስዋዕትነት፣ ትብብር እና የማይናወጽ ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ የተስፋ ብርሃንም ነው ብሏል ፌዴሬሽኑ። ሕዳሴ የጋራ ጥረት፣ ፅናት እና አንድነት ሲደመሩ ታላቅነትን እንደሚወልዱ ያመላከተ፣ የሀገርን አቅምም ያሳየ ፕሮጀክት ነው።
“እንደ አማራ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን በዚህ ታሪካዊ ስኬት የተሰማንን ደስታ እና ኩራት እንገልጻለን” ሲልም አስፍሯል ፌዴሬሽኑ። ሕዳሴ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለውጥ፣ ማኅበራዊ ልማት እና የቴክኖሎጂ እድገት የማዕዘን ድንጋይ መኾኑን በውል መገንዘብ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፏል።
ይህንን ሀገራዊ ሃብት በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና በወጉ በማስተዋወቅ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ እንደወጣት ራስን እስከመስጠት ድረስ እንሠራለንም ብሏል የፌዴሬሽኑ መግለጫ።
የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ ሁሉም ወጣቶች አንድነታቸውን ማጠናከር፤ በቴክኖሎጅና ፈጠራ ራሳቸውን ማብቃት እንዲሁም በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸውም ጥሪ ቀርቧል።
የሕዳሴ ግድብ መመረቅ የልማት ጉዟችን ፍጻሜ አይደለም፤ ይልቁንም በኢትዮጵያ የአዲስ ታሪክ ምዕራፍ ጅምር ነው ብሏል መግለጫው። ሕዳሴ የኢትዮጵያውያን ኩራት፣ የወጣቶች ጥንካሬ እና የአፍሪካም ጭምር ተስፋ ስለመኾኑም ተጠቁሟል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!