
ባሕር ዳር፡ መስከረም 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አዲስ ከተመረጠው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መሪዎች ጋር ዛሬ ተወያይተናል ብለዋል።
በዚሁ አጋጣሚ ሀገር አቀፍ የመጅሊስ ምርጫው በተሳካ መልኩ እንዲካሄድ በማድረጋቸው ለሕዝበ ሙስሊሙና ለምክር ቤቱ መሪዎች አድናቆቴን ለመግለጽ እወዳለሁ ነው ያሉት።
የመጅሊስ ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ፣ አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ መከናወኑ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
መንግሥት ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መሪዎች ጋር በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ተቀራርቦ እንደሚሠራ ገልጸዋል። በሚያስፈልገው ሁሉ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ለምክር ቤቱ መሪዎች መልካም የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንላቸው እመኛለሁ ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!