ምርትን ለውጭ ገበያ እያቀረበ ያለው የባሕር ዳር ልዩ ኢኮኖሚ ዞን

1
ባሕር ዳር፡ መስከረም 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በጊዜ ሂደት ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለምታደርገው ሽግግር ተስፋ ከተጣለባቸው ዘርፎች መካከል የኢንዱስትሪ ዞኖች የላቀውን ሚና ይጫዎታሉ።
ለዚህም ሲባል በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ የተቋቋሙ የኢንዱስትሪ ዞኖች ወደ ሥራ ከገቡ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሽግግሩን በማምረት፣ በአቅም፣ በዕውቀት፣ በቴክኖሎጅ እና በተወዳዳሪነት ለመምራት እንዲቻል ግዙፍ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ በተለያዩ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ዞኖች ተቋቁመው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
ከተቋቋሙት የኢንዱስትሪ ዞኖች ውስጥ አንዱ የባሕር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ነው፡፡
የባሕር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ጥቅምት 2010 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ በ2012 መጨረሻ መጠናቀቁን እና የርክክብ ሥራው ተፈጽሞ ባለሃብቱ ወደ ሥራ መግባቱን የባሕር ዳር ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዋና ሥራ አሥኪያጅ ጥሩዬ ቁሜ ተናግረዋል፡፡
የግንባታ ሥራው 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ወጭ እንደተደረገበት የተናገሩት ሥራ አሥኪያጇ በውስጡ ስምንት ሸዶች እንዳሉትም አብራርተዋል።
በመጀመሪያ ሲገነባ የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ የሀገር ውስጥ ምርትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የዶላር እጥረትን ለመቅረፍ ታሳቢ ያደረገ እና ለውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ነበር ብለዋል፡፡
በዚህም ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ከ2014 ጀምሮ እስካሁን ባለው ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉ ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገር መላካቸውን የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዋና ሥራ አሥኪያጇ ተናግረዋል።
ተኪ ምርቶችን በተመለከተ 7 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር የሚያዎጣ የሀገር ውስጥ ተኪ ምርት ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ቀርቧልም ነው ያሉ።
ሥራ አሥኪያጇ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ከአርሶ አደሮች እና ከሸማች ማኅበራት ጋር አምራች ድርጅቶች የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋልም ብለዋል።
አሁን ላይ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በዋናነት ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ትኩረት የሰጠ፣ ከጨርቃ ጨርቅ አልባሳት ወጥቶ በሌሎች የሥራ ዘርፎች ላይም ትኩረት በማድረግ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ማኑፋክቸሪንግ እና ሌሎችም የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ እንዲሠራ እየተደረገም ይገኛል።
የኢኮኖሚ ዞኑ በውጭ ባለሃብቶች ብቻ አለያም ወደ ውጭ ብቻ በመላክ ሳይታጠር የሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች እንዲቀርቡ እና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ይህ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሲቋቋም በዓመት 13 ሺህ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ታሳቢ መደረጉንም ነው ሥራ አስኪያጇ ያብራሩት።
ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ፓርኩ መጥቶ ኢንቨስት ለማድረግ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ሥራ አሥኪያጇ የኢኮኖሚ ዞን ፓርኩ የተሟላ የመብራት ኀይል አቅርቦት፣ በቂ የውኃ ቦቲ፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ፣ የተደራጁ እና ብቁ የኾኑ የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ፣ የተሟላ ክሊኒክ፣ አምቡላንስ፣ የተደራጀ ዳታ ቤዝ፣ 24 ሰዓት የሚሠራ ሲሲቲቪ ካሜራ፣ ጽዱ እና ውብ የኾነ ግቢ ከተሟላ የጥበቃ አገልግሎት ጋር ማሟላቱንም ጠቅሰዋል፡፡
ባለሃብቶች የሚፈልጉትን ዋና ዋና ምቹ ሁኔታዎች የኢኮኖሚ ዞን ፓርኩ እንዳሟላ የተናገሩት ሥራ አሥኪያጇ በቀጣይም ባለሃብቶች በሚሰጡት አስተያየት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ምቹ የማድረግ ሥራ ይሠራልም ብለዋል።
የኢኮኖሚ ዞን ፓርኩ አሁን ያልተያዙ ሸዶችን ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ለመስጠት ከውጭ ባለሀብቶች በተለየ የማበረታታት ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
ምርትን ወደ ውጭ ከመላክ ባለፈ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ሰፊ ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
የውጭ ባለሃብቶችን ብቻ ከመናፈቅ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ገብተው እንዲሠሩ እና የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ተናግረዋል። በዚህም የሀገር ወስጥ ባለሃብቶች የተሻለ ሥራ ሠርተዋል ነው ያሉ፡፡
ለዚህም እያንዳንዱ ፓርክ ካለበት ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት እና የአካባቢ ጸጋዎችን በመጠቀም በ2030 የሠለጠነ የሰው ኀይል እና ቴክኖሎጅን በመጠቀም የተሻለ ገቢ ለማስገኘት ሥራ እንደሚሠራም ነው ያብራሩ።
በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ስምንት የማምረቻ ሸዶች መኖራቸውን የተናገሩት ሥራ አሥኪያጇ ሸዶቹ እያንዳንዳቸው 5 ሺህ 500 ካሬ ላይ ያረፉ ናቸው ብለዋል፡፡
ከስምንቱ ሸዶች አምስቱ በባለሃብቶች ተይዘው ሥራ እየተሠራባቸው መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡ ከአምስቱ ባለሃብቶች ሦሥቱ ባለሃብቶች እስከነችግሩም ቢኾን ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ስለመኾናቸው ጠቁመዋል።
በቀጣይም ያልተያዙ ሸዶች እንዲያዙ እና የለማውን መሬት ለማስያዝ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ባለሃብቱ በሚፈልገው ልክ ለማስተናገድ እንደሚሠሩም ነው ያብራሩት፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየፌዴራል እና የጎንደር ከተማ ከፍተኛ መሪዎች በጎንደር ከተማ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን እየተመለከቱ ነው።
Next articleመሪዎች ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን በመረዳት የሀገሪቱን ዕድገት ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ይገባቸዋል።