ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዘመኑ ትውልድ የጋራ እና የወል እውነት መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ። 

6

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 4/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምረቃን አስመልክቶ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

ሕዳሴ የሀገራችን የማንሰራራት ጅማሮ ማሳያ፤ የዘመኑ ትውልድ የጋራ እና የወል እውነት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የመላ ኢትዮጵያውያን የኅብረት እና የአንድነታችን ማረጋገጫ፣ የአብሮነታችን ምስክር፣ የእድገታችን መዳረሻ መንገድ ኾኗል ብለዋል።

 

ርእሰ መሥተዳድሩ በመልዕክታቸው ፈተናዎችን ሁሉ በትዕግስት እና በትጋት አልፈን ለድል እና ስኬት በቅተናል ነው ያሉት። አንድ ኾነን የዘመናት ቁጭታችንን በልፋት እና ጥረታችን ወደሚጨበጥ ብርሃን መቀየር ችለናል። በራሳችን ወረት፣ በደም እና በላባችን ዘመን ተሻጋሪ እና ትውልድ አስከባሪ ትልቅ መሠረት አስቀምጠናል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያዊያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ፍላጎት ልማት እና ለውጥ፤ እድገት እና ብልጽግና መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የታላቁ ሕዳሴ ግድብም የሀገራችን እድገት እና ብልጽግና መስፈንጠሪያ ነጥብ ነው።

 

ከኃይል ማመንጨት ባሻገር ለየትኛውም ችግር አይበገሬነታችንን ያረጋገጥንበት ፕሮጀክት ነው። ታላቁን ፕሮጀክት አጠናቅቀን ችለን አሳይተናል፤ ለሀገራችን እድገት ትልቅ አቅም ኾኗል ብለዋል።

 

ሕዳሴ እንደሀገር የኃይል አቅርበት ችግር በዘላቂነት ይፈታል። የሕዝባችን ጥቅም እና ፍላጎት ያረጋግጣል። የግድቡ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያዊያን ታላቅ ኩራት፤ ለቀጠናው ሀገራት ደግሞ ትልቅ ትርጉም አለው። የአጎራባች ሀገራትን ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ይፈጥራል።

 

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ሁሌም የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው። ዛሬም እንደትናንቱ ለሀገር ክብር እና ሰላም በአንድነት በመቆም ለሌላ ድል በጋራ መስራት ይኖርብናል።

 

ታላቁ ሕዳሴ ግድብ እውን እንዲሆን አመራር ለሰጡ፣ ላቀዱ፣ ፕሮጀክቱን ለመሩ፣ ላስተባበሩ እንዲሁም በሀገር ፍቅር ስሜት ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በግድቡ ግንባታ ለተሳተፉ ሰራተኞች ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ።

 

በመጨረሻም ርእሰ መሥተዳድሩ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን ብለዋል።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሕዳሴ ግድቡ የታሪካችን እጥፋት እና ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ የሚወስድ ፕሮጀክት ነው” የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት
Next article“ጎንደር ከጉስቁልና ወጥታ እያንሠራራች ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው