
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ተመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።
የባርባዶስ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞትሊ ይህ የኢትዮጵያን እና የአካባቢውን ሕዝብ ያንቀሳቀሰ ታሪክ ነው ብለዋል። ለቀጣናው የብልጽግና መስፈንጠሪያ መኾኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያኮራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሁሉንም ፍላጎቶችን ተቋቋመው የሠሩት ሥራ ነው ብለዋል።
ይህ የዓድዋ የምሕንድስና ጥበብ የታየበት መኾኑንም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጫናዎችን ተቋቁሞ የሠራው ታላቅ ፕሮጀክት መኾኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ከማንም ምንም ሳይጠብቁ የሠሩት ፕሮጄክት እንደኾነም አንስተዋል።
ይህ ፕሮጄክት አፍሪካውያን እንደሚችሉ ያሳየ መኾኑንም ገልጸዋል። ዛሬ ኢትዮጵያ ችላ ማሳየቷንም ተናግረዋል።
የካሪቢያን ሀገራት እና የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ ከገለጠችው የይቻላል መንፈስ ትምህርት እንዲወስዱም አሳስበዋል።
በአንድነት፣ ለአንድ ዓላማ፣ ለአንድ ግብ እና ለአንድ መዳረሻ መደደፊት እንሂድ ብለዋል በመልዕክታቸው። ለኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።
የኢስዋትኒ ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር ራስል ሚሚሶ ድላሚኒ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ ብለዋል። የሕዳሴ ግድብ ብልሃት የተሞላበት እና የአመራር ጥበብ የታየበት እንደኾነም ገልጸዋል።
የመሪዎች ጥበብ እና የሕዝቡ አንድነት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን እውን እንዳደረገው ነው የተናገሩት። “ዛሬ እናንተ ባሳካችሁት ስኬት አፍሪካ ትኮራለችም” ነው ያሉት።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐመድ አሊ የሱፍ የዛሬው ቀን የኢትዮጵያ ቀን ነው ብለዋል። የሕዳሴው ግድብ የሕልም፣ የጠንካራ ሥራ እና ብልሃት የተሞላበት አመራር ውጤት መኾኑንም ገልጸዋል።
የሕዳሴ ግድብ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ ለኤሌክትሪክ ኀይል እና ለሌሎች ልማትም ትልቅ አቅም እንዳለው ነው የተናገሩት።
ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ደማቸውን እና ላባቸውን ሰጥተው ሕዳሴ ግድብን ለሠሩ ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ነው ያሉት።
ይህ የሚያስደንቅ ስኬት ነውም ብለዋል።
የአፍሪካ 2063 አጀንዳ ዜጎችን በመሠረተ ልማት፣ በኀይል አቅርቦት እና በሌሎች ውጤታማ ማድረግ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግቡን ለማሳካት ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል አንደኛው እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ዘጋበ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!