ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሌላኛው ሰንደቅ ዓላማችን ነው።

2
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራሳችን የገንዘብ አቅም ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ መንግሥት ሠራተኛ፣ ከአርሶ አደር እስከ ተመራማሪ፣ ከጉልት ነጋዴ እስከ አስመጭ እና ላኪ የታተሩበት ነው።
ከገጠር ነዋሪው እስከ ዲያስፖራው፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ድረስ ብቻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለው አቅም የሚችለውን ሁሉ ያሳረፈበት የዚህ ዘመን ትልቅ አሻራ ነው ማለት ይቻላል።
ግድቡ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ሲኾን በተለይም በገጠራማው የሀገራችን ክፍል የሚኖሩ በርካታ ወገኖቻችን የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል።
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገሮች በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝም ነው፡ከኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭነት ባለፈ ለመስኖ እና ዓሳ ሃብት ልማት፣ ለመጓጓዣ፣ ለቱሪዝም እና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ጉልህ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ ግድብ የግንባታ ሂደት የሀገራችን ሕዝብ አንድነት ጎልቶ የታየበት፤ ሕብረ ብሔራዊነት የተንጸባረቀበት፣ በታሪክ የምናውቀውን የዓድዋ ድል በዘመናችን የተደገመበት የኩራታች ምንጭ ልንለውም እንችላለን፡፡ ግድቡ ከተጀመረ ከ14 ዓመታት ቆይታ በኋላ ተጠናቅቆ በዛሬው ዕለት ጳጉሜን 04/2017 ዓ.ም ለምረቃ በቅቷል ፡፡
የግድቡ መጠናቀቅ እና መመረቅ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ፈጥሯል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ያነጋገርናቸው ወጣቶች ሃሳባቸውን እና ስሜታቸውን አጋርተውናል፡፡
ወጣት መለሰ ዓለሙ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን “በማይተካ ነፍስ የተሞሸረ በደም ቀለም የተጻፈ ታሪክ ያያዘ ቅርሳችን ነው” በማለት ገልጾታል፡፡ አንድነታችን፣ ሕብረ ብሔራዊነታችንና ወንድማማችነታችንን የሚገልጽ እንደኾነ ነው የተናገረው፡፡ የሀገራችን ሕዝብ ባለው አቅም ቦንድ በመግዛት አሻራውን ያሳረፈበት መኾኑንም አንስቷል፡፡
ግድቡ በብዙ ውጣ ውረዶች በጽናት ነው ከዚህ የደረሰው ያለው ወጣት መለሰ ይህም ኢትዮጵያውያን ስንተባበር ምንም ችግር የማይበግረን ለመኾኑ ማሳያ ነው ብሏል፡፡ ከዚህም ወጣቱ ጽናትን፣ አንድነትን እና ሞጋችነትን ተምረንበታል በማለት አንስቷል፡፡
ሌላኛዋ ወጣት ትዕግስት ታድሎ የሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቁ ደስታዋን ገልጻለች፡፡ “ግድቡ የሀገራችን እና የሕዝባችን ኩራት እና ሌላኛው ሰንደቅ ዓላማ ነው“ በማለት ነው የገለጸችው፡፡ ምክንያቱም በብዙ ፈተና ውስጥ፣ የኢትዮጵያን መበልጸግ እና ማደግ የማይፈልጉ አካላትን የክፋት አስተሳሰቦች እና መድረኮችን ያለፈ ነው ብላለች፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግና እና ለተሰለፈበት ዓላማ ቁርጠኛ ውሳኔ የሚሰጥ የልማቱ ተሳታፊ በመኾኑ ግድቡን እንደ ዐይኑ ብሌን በመጠበቅ የሚችለውን ሁሉ አስተዋጽኦ በማበርከት ለዚህ አድርሶታል ነው ያለችው፡፡
ይህ ግድብ የነገዋን ኢትዮጵያ ህልውና የሚያስጠብቅ እና ሊያሻግር የሚችል እንደኾነ ጠቁማለች፡፡ እንደ ግድቡ ሁሉ ከተባበርን ሌሎች የልማት ሥራዎችን መከወን የምንችል መኾኑን የሚያረጋግጥ እና የሚያመላክት እንደኾነም ነው የተናገረችው፡፡
በግድቡ ላይ ወጣቶች በቦንድ ግዥ እና ለሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ቦንድ እንዲገዛ በመቀስቀስ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ በቀጣይም በሀገራችን እና በክልላችን ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ትምህርት የተወሰደበት እና አቅማችን የታየበት እንደኾነም ገልጻለች፡፡
በተመሳሳይ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ሃሳቡን የገለጸልን ወጣት አስራት መኳንንት በግድቡ መጠናቀቅ ደስታውን ገልጾ ከነበሩበት መሰናክሎች ወጥቶ መጠናቀቁ በጽናት ከቆምን ከግብ መድረስ እንደምንችል የተማርንበት ነው ብሏል፡፡
የግድቡ መጠናቀቅ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል አስተዋጽኦው ከፍተኛ መኾኑንም አመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ጳጉሜ 4 “የማንሰራራት ቀን”ን በመሠረተ ልማት ጉብኝት እያከበረ ነው።
Next articleየወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ መመረቅን አስመልክቶ ደስታቸውን ገለጹ።