
አዲስ አበባ: ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንበረት ጉባኤ መክፈቻ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የአየር ንብረት ለውጥ የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ብቻ ሳይኾን ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶ መኾኑን ተገንዝቦ መንቀሳቀስ ይጠይቃል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ዓላማ አንግባ ከሕዝቦቿ ጋር በዘርፉ ትልቅ ስኬት አምጥታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) 48 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ተጨባጭ የኾነ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔን አሳይታለች ነው ያሉት።
የሌማት ትሩፋት ሥራም በአየር ንብረት ለውጥ የማይናወጥ የምግብ ሥርዓት ለመገንባት እና ራስን ለመቻል ኢትዮጵያ የነደፈችው ትልቅ መፍትሔ እንደኾነም ጠቁመዋል። ይህም ለውጥ ማምጣቱን ነው ያስገነዘቡት።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን የሚፈታ ትልቅ ፕሮጀክት መገንባቷንም ነው ያብራሩት።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የታዳሽ ኀይል ምንጭ በመኾን የዘርፉን ችግር የሚፈታ አይነተኛ መፍትሔ እንደኾነም ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀገራቸው ከተሞችን አረንጓዴ፣ ለመኖር ምቹ፣ መኪኖችን በኤሌክትሪክ የሚሠሩ በማድረግ ወሳኝ መፍትሔዎችን እየሠራች እንደኾነም ጠቁመዋል።
በ2030 አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን አልፋ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ እና በሥራ ፈጠራ በማሳደግ የተሟላ መፍትሔ ያላት አህጉር ለማድረግ ኢትዮጵያ ጠንክራ እንደምትሠራም አረጋግጠዋል።
ለአረንጓዴ አየር ንብረት ዋጋ መስጠት እና የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲኾንም መሥራት ይገባል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)።
“ነገ ሳይኾን አሁን የተደመረ መፍትሔ የምናመጣበት ጊዜ ነው፤ ንፁህ አየር የሚተነፈስበት ሁኔታ በመፍጠር አፍሪካ ብቻ ሳይኾን ሁሉም የቀጣይ ትውልድ ንፁህ አየር የሚተነፍስበት ዓለም አንፍጠር” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን