
አዲስ አበባ: ጳጉሜን 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ለምርቃት ዝግጁ ኾኗል ብለዋል። ግድቡ በፋይናንስ ምንጩ፣ በሚይዘው የውኃ መጠን እና በፈጠረው ብሔራዊ አንድነት ከሌሎች የኃይል ማመንጫዎች ልዩ እንደኾነ ገልጸዋል።
እስካሁን ያለው የግድቡ ግንባታ ወጭ ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ መኾኑን በመግለጫው አንስተዋል። ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት መሸፈኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከዚህ ውስጥ 91 በመቶው በመንግሥት እና ቀሪው በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተገኘ መኾኑን ተናግረዋል።
ከገንዘቡ ድጋፍ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ በዕውቀት፣ በዲፕሎማሲ፣ በጉልበት እና በሃሳብ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው በመግለጫቸው አብራርተዋል። ይህም ግድቡ በጫናዎች ሳንበገር በፍትሐዊነት እና በራስ አቅም የመልማት እና “ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጽኑ ፍላጎታችንን ለዓለም ያሳየ ነው” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ረህመት አደም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!