ጽናት ከቀደምት አባቶቻችን የወረስነው የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው።

2
ጎንደር: ጳጉሜን 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር “ጽኑ መሠረት፣ ብርቱ ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት የጸጥታ አካላት “የጽናት ቀንን” አክብረዋል።
የፀጥታ አካላቱ በወታደራዊ አጀብ እና ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት በማካሄድ ነው ቀኑን ያከበሩት።
‎በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ አባላት ተሳትፈዋል።
‎የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አለልኝ ዓለም ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሟትም በልጆቿ አንድነት እና ጽናት መከበር መቻሏን ተናግረዋል።
‎ኢትዮጵያ በልጆቿ ደም እና አጥንት ነጻነቷን ያስከበረች እና ተከብራ የኖረች ጽኑ ሀገር መኾኗንም አስገንዝበዋል።
‎‎ቀደምት አባቶች አጽንተው ያቆሟትን ሀገር በጽናት ጠብቆ ለትውልድ ማሻገር እንደሚገባም ኀላፊው ገልጸዋል።
‎የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ 105ኛ ጠቅላላ አገልግሎት ኀላፊ ኮሎኔል ዓባይ በላቸው “ጽናት ከቀደምት አባቶቻችን የወረስነው የሀገር ፍቅር መገለጫ ነው” ብለዋል።
‎ጽናት እና መስዋዕትነት ጀግንነት ነው ያሉቶ ኮሎኔል ዓባይ ኢትዮጵያ እየተጓዘችበት ላለው የስኬት ጉዞ በጽናት መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።
‎በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ የጎንደር እና አካባቢው የጸረ ኮንትሮባንድ ሬጅመንት አዛዥ ኮማንደር አሰፋ አበበ “ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ያላት ሀገር ናት” ብለዋል። ‎ሠራዊቱም ኢትዮጵያን በጽናት የሚጠብቅ መኾኑን ተናግረዋል።
‎ጽናት ለጸጥታ አካላት ልዩ ትርጉም አለው ያሉት የጸጥታ አባላቱ ጽናት ለሀገር መሠረት መኾኑንም ተናግረዋል።
ለሀገር መስዋዕዋትነት መክፈል ለጸጥታ አካላት ክብር ነው ያሉት በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል የሰሜን ምዕራብ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሬጅመንት አምስት አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ ገላው ናቸው። የጸጥታ አካላት ሁሌም ሀገርን በክብር ከፊት የሚያቆሙ ስለመኾኑም ነግረውናል።
‎ኢትዮጵያ የጽኑ ሕዝብ ባለቤት መኾኗን ያነሱት ደግሞ በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ የሰው ኃይል ልማት አዛዥ ምክትል ኮማንደር አያል ተገኘ ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በጽኑ መሠረት የገነባትን ሀገር ጠብቆ በክብር ለትውልድ ማስረከብ ይገባልም ነው ያሉት።
‎ዘጋቢ:- ‎ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሕዳሴ ግድብ ምረቃ ዋዜማ ላይ ኾነን “የጽናት ቀንን” ማክበራችን ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው።
Next article“የጽናት ቀን” በወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተከበረ።