
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ “የአፍሪካ ወጣቶች የአየር ንብረት ጉባኤ 2025ን” አስጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት ወጣቶች ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር አፍሪካን የሚገነቡ መሐንዲሶች ናቸው ብለዋል።
ዛሬ ወጣቶቻችን የመጪው ዘመን የአየር ንብረት አጀንዳዎች የሚቀርጹበትን “የአፍሪካ ወጣቶች የአየር ንብረት ጉባኤ 2025”ን በመዲናችን አዲስ አበባ ከፍተናል ነው ያሉት።
አፍሪካ ለበካይ ጋዝ ልቀት ያላት አስተዋጽኦ ዝቅተኛ መኾኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በድርቅ፣ በበረሃማነት፣ በምግብ ዋስትና ችግር፣ በጎርፍና በሌሎች አደጋዎች እየተፈተነች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
አህጉራችን አፍሪካ ችግሮች ቢደራረቡባትም የተጨባጭ መፍትሔዎች አህጉር መኾኗ የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ትግበራና ስኬት ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢኒሺየቲቭ በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 48 ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን ተክላለች፤ ለሚሊዮን ወጣቶቿ የሥራ ዕድል ፈጥራበታለች፤ የምግብ ዋስትናንም ማረጋገጥ ጀምራለች ነው ያሉት።
ሀገራችን ለቀጣናው ታዳሽና የንጹሕ ኢነርጂ እያቀረበች መሆኗም አፍሪካ በሕዝቦቿ ንቁ ተሳትፎ ራዕይዋን እንደምታሳካ ተጨባጭ የተግባር ምሳሌ ነው።
ወጣቶች የአፍሪካ የጥንካሬና የተስፋ ምንጭ በመሆናቸው የማትበገር አፍሪካን ለመገንባት ፈጠራ መር መፍትሔዎችን በማፍለቅና በትብብር መሪ ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን