
ባሕር ዳር: ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት ሥራ አስጀምረዋል።
የአቅመ ደካሞች የቤት ሥራው በአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ አማካኝነት የሚሠራ ነው።
የቤት ሥራው የተጀመረላቸው እማሆይ ፀሐይ አምባው ቤታቸው በደርግ ዘመነ መንግሥት ጊዜ እንደተሠራ ተናግረዋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሳይታደስ መኖሩን ገልጸዋል።
ቤቱ ረጅም ጊዜ በመቆየቱ በበጋ ፀሐይ፣ በክረምት ዝናብ ያስቸግራቸው እንደነበር ተናግረዋል። አሁን ግን በአዲስ ዓመት ዋዜማ ብርሃን መጣልን፣ ከአዲሱ ዓመት መምጣት ጋር አዲስ ነገር አየን ነው ያሉት።
አሁን ብሞትም በጥሩ ቤት ሬሳዬ ይሸኛል፤ ደስታየ ታላቅ ነው ብለዋል። እንደኔ አቅመ ደካማ የኾኑ ወገኖቼ እንዲሠራላቸውም እፈልጋለሁ፤ አቅም ያላቸው እጃቸውን ይዘርጉላቸው ብለዋል።
ሌላኛዋ የቤት ሥራ የተጀመረላቸው እናት ብርቄ ዋለ የእርሳቸውም ቤት በደርግ ዘመን እንደተሠራ ተናግረዋል። እድሳት ሳይደረግለት እንደኖረም ገልጸዋል። አሁን ግን በቅኖች ታይተናል፤ ደስ ብሎናልም ብለዋል። በአዲሱ ዓመት አዲስ ቤት ልናይ ነው፤ ይባረኩ ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን ቤት የመጠገን እና በአዲስ መልክ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
108 ቤቶችን ጠግነው፣ 70 ቤቶችን ደግሞ በአዲስ ሠርተው ማስረከባቸውን ተናግረዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። ከቤት እድሳት እና ሥራ ባለፈ የደም ልገሳ፣ ለተማሪዎች ቁሳቁስ ድጋፍ እንደተደረገ ነው የተናገሩት። የአዲስ ዓመትን መግባት ተከትሎ ለአቅመ ደካሞች የበዓል መዋያ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ላሳየው በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል። በከተማዋ በርካታ የልማት ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) ዛሬ የተጀመረው የቤት ሥራ የዓመቱ የመጨረሻ የበጎ አገልግሎት መኾኑን ገልጸዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የኢትዮጵያውያን እንቁ ባሕል እና እሴት መኾኑን ተናግረዋል። ይህም መልካም እሴት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመንግሥት ልዩ ትኩረት ኾኖ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባሕል እንዳደረገም ተናግረዋል። 15 ሚሊዮን ብር በማውጣት 41 ቤቶችን ገንብተው ማስረከባቸውንም ገልጸዋል። ዛሬ የተጀመረው ደግሞ ተጨማሪ ነው ብለዋል።
ከቤት ጥገና ባለፈ ለተማሪዎች ቁሳቁስ የማቅረብ፣ ደም የመለገስ እና ሌሎች የሰብዓዊ ተግባራትን መፈጸማቸውን ተናግረዋል። ለተማሪዎች ቁሳቁስ 28 ሚሊዮን ብር ወጪ ማደረጋቸውንም ገልጸዋል። በአጠቃላይ በዓመቱ 84 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ መሥራታቸውን ነው የገለጹት።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሥራ እና ሥልጠና ሥራ ከባድ፣ የብዙ አካላትን ትብብር የሚጠይቅ፣ በአንድ ተቋም ብቻ የማይሠራ፣ የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ቁልፍ ተግባር የሚፈጸምበት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አንደኛው ችግር ሥራ አጥነት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የሥራ እና ሥልጠና ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል። የአማራ ክልል የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅድ በማቀድ የተሻለ ክልል ለመፍጠር ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ በአሻጋሪ እድገት እና በዘላቂ ልማት እቅዱ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል ብለዋል። የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የወጣቶች ክህሎት እንዲያድግ፣ በእውቀት የሚመሩ እና የሚሠሩ መሪዎችን እንዲፈጥር ተልዕኮ የተሠጠው መኾኑን ተናግረዋል። የሰው ኃይል በኢኮኖሚ ውስጥ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የሚያግዝ መኾኑን ገልጸዋል። ትልቅ ተልዕኮ የተሸከመ፣ የበርካታ ተቋማትን ተግባር በውስጡ የያዘ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በክልሉ ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ መጀመሩን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት። በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አይተናል ብለዋል።
ወደፊታችን ተስፋ አለ ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሰላማችን እያረጋገጠን ልማታችን እናፋጥናለን ነው ያሉት። መሪዎች እና ባለሙያዎች በቁርጠኝነት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን