ሕዝቡ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ስሜቱን የሚገልጽበት አጭር የጽሑፍ መላኪያ ይፋ ተደረገ።

43
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያውያን አብሮነት ያለ ምንም የውጭ ድጋፍ የተገነባው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ ኅብረተሰቡ ለግድቡ ያለውን ደስታ የሚገልጽበት አጭር የጽሑፍ መልዕክት መላኪያ ይፋ ተደርጓል።
የመልእክት ማስቀመጫው ‘የትውልድ አሻራ’ በሚል ስያሜ ነው ይፋ የተደረገው።
ይህን ሥራ በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት እና በኢትዮ ቴሌኮም ትብብር ይፋ መደረጉን የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አረጋዊ በርሄ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ዶክተር አረጋዊ በርሄ እንዳሉት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ “የዚህ ዘመን ዓድዋ” ሲኾን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት አሻራቸውን ያኖሩበት የአንድነት ሃውልት ነው።
ግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ከመጋቢት 24/2003 ዓ.ም. ጀምሮ ከኢትዮጵያውያን ከ23 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ተሠብሥቧል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ያላቸውን አዎንታዊ ስሜት፣ ግድቡ በሕይወታቸው ያለውን ተጽዕኖ እና ሌሎችንም መልዕክቶች በአጭር የጽሁፍ መልዕክት (SMS) በ8120 መላክ ይችላሉ ነው የተባለው።
እነዚህ ዲጂታል መልዕክቶች ታሪክ ኾነው የሚዘክሩ እና ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፉ ይኾናሉም ብለዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ መሳይ ውብሸት ኢትዮ ቴሌኮም ከግድቡ ግንባታ መጀመሪያ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ላበረከተው አስተዋፅኦ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
በዚህ አዲስ ፕሮጀክት ላይም ተሳታፊ በመኾናቸው መደሰታቸውን ነው የተናገሩት።
‘የትውልድ አሻራ’ ፕሮጀክት ከነሐሴ 27/ 2017 ዓ.ም እስከ መስከረም 30/ 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይም ነው የተብራራው።
ከፕሮጀክቱ ጎን ለጎን የተለያዩ የፓናል ውይይቶች፣ የሥዕል ዐውደ ርዕይ እና ሕዝባዊ መድረኮችም እንደሚዘጋጁ ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ሰላማዊት ነጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ያንሠራራችበት ዓመት በመኾኑ ጳጉሜ 4 የማንሠራራት ቀን በሚል ይከበራል።
Next articleየኢትዮጵያን ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ መንግሥት ለጥራት ትኩረት ስጥቶ እየሠራ ነው።