
ባሕር ዳር:ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ከ2018 እስከ 2042 የሚተገበረውን “የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ በላቀ የአመራር ቁርጠኝነት እና ትብብር ለመፈጸም የሚያስችለውን “የጎርጎራ ቃልኪዳን” ሰነድን ፈርመው ለዞን አሥተዳዳሪዎች እና ለከተማ ከንቲባዎች ሰነዱን አስረክበዋል።
ሰነዱ በጎርጎራ የተሰየመበት ምክንያት አካባቢው እምቅ ጸጋ እያለው በልኩ ሳይለማ የቆየ እና አሁን ግን ሲለማ ውበቱ የተገለጠ መኾኑን ለማሳየት እና መሥራት ሥንችል መለወጥ እንደምንችልም ለማስገንዘብ ነው ብለዋል።
የተገለጠው የጎርጎራ ውበት የመጭውን የክልሉን ሕዝብ የልማት ራዕይ የሚገልጽ በመኾኑም ሰነዱ “የጎርጎራ ቃል ኪዳን” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
ሰነዱ የአሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ ልማት እቅዱን ለማሳካት የወቅቱ መሪዎች ቃል የገባንበት ነው ብለዋል። ቃል ኪዳኑ የወቅቱ አመራሮች በትጋት እንዲፈጽሙ እና ተተኪ ወጣት አመራሮችንም በማፍራት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው ብለዋል።
ቃልኪዳኑን የፈረሙ መሪዎች፣ በተዋረድ የሚገኙ አመራሮች እና መላው የመንግሥት ሠራተኞች እና ሕዝብ ለእቅዱ መሳካት መረባረብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ይህ ቃል ኪዳን የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ እድገት የሚረጋገጥበት፣ መልካም አሥተዳደር የሚሰፍንበት ሀገራዊ አንድነት ከፍ የሚልበት እና ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚረጋገጥበት በመኾኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እና አልቆ መተግበር ይገባዋል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅዱ ሁሉን አካታች በኾነ መልኩ ተሳትፎ ተደርጎበት እና ዳብሮ የወጣ ነው፤ ይህንን እቅድ ለመፈጸም ሕዝብን እና በየደረጃው የሚገኙ መሪዎችን የሚወክሉ ከፍተኛ መሪዎች በተገኙበት የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈርሟል ብለዋል።
“ቃል የገባ ሰው አይለያይም፤ በጋራ ሠርቶ በጋራ ያድጋል” ያሉት አቶ ይርጋ ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ መሪዎች “ጎርጎራ ቃል ኪዳን” እንዲሳካ ጥረት ማድረግ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!