
አዲስ አበባ: ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥራትን በማስጠበቅ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
የአሥተዳደሩ ትምህርት ቢሮ 32ኛው ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባኤ “በዕውቀት እና በክህሎት ትውልድን በማፍራት ኢትዮጵያን ተምሳሌታዊ ሀገር እናደርጋለን” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳሉት ከተማ አሥተዳደሩ በዕውቀት እና በክህሎት የታነጸ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችሉ ርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።
ለጥራት አጋዥ የኾኑ እና የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ውጤት ተገኝቷል።
በዚህም በዕውቀት እና በአካል የዳበረ ትውልድ ለማፍራት የትምህርት ቤቶችን ገጽታ በመቀየር እና በቴክኖሎጂ በማገዝ የመማር ማስተማሩን ሥራ ማካሄድ ተችሏል ነው ያሉት።
ጥራትን ለማረጋገጥ ትምህርት ቤቶችን የማደስ፣ የመገንባት እና ምቹ የመማር ማስተማር ሁኔታ የመፍጠር፣ የትምህርት ቤት ምገባ እና ሌሎች ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
ለትምህርት ጥራት ትኩረት በመስጠት በተለይም በቅድመ መደበኛ ትምህርት የነገ ትውልድን ለመገንባት ያስቻሉ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ.ር) ከተማ አሥተዳደሩ በሰጠው ልዩ ትኩረት ለትምህርት ዘርፉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን ውጤታማ የመማር ማስተማር ሁኔታ እንዲኖር የባለድርሻ አካላት ቅንጅት የበለጠ መጠናከር እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ እንዲኾኑ እና ከአዋኪ ድርጊቶች እንዲጸዱ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።
በትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ እና የቁሳቁስ አቅርቦት መካሄዱ ተማሪዎች በስፋት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ ማስቻሉንም ከንቲባዋ ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሐመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን