ብሔራዊ የጥራት መንደር ንግድ እና ኢንቨስትመንትን በማሻሻል እያገዘ ነው።

13
አዲስ አበባ: ነሐሴ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በጥራት መንደር የተዘጋጀውን “የኢትዮጵያን ይግዙ” ሀገራዊ የንግድ ሳምንት ኤክስፖ ከፍተዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚቆየው ኤክስፖ የተዘጋጀውን ኤግዚቪሽን እና ባዛር ተዘዋውረውም ጎብኝተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የላቀ አፈፃጸም ላስመዘገቡ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የዕውቅና እና ምሥጋና መርሐ ግብርም ተካሂዷል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) እንዳሉት የሚኒስትር መስሪያ ቤቱን አገልግሎት ፈጣን እና ምቹ ለማድረግ የሥራ ከባቢን ምቹ እና ሳቢ ማድረግ ተችሏል።
በ2017 በጀት ዓመት 3 ሚሊዮን 25 ሺህ 767 የንግድ ምዝገባ እና ፍቃድ አገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማገዝ ማከናዎን እንደተቻለም አስገንዝበዋል፡፡
3 ሚሊዮን 117 ሺህ 920 የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ስለመከናወኑም ነው የጠቆሙት።
የኅብረተሰቡን የኑሮ ውድነት ለመፍታት የቅዳሜ እና እሑድ ግብይት ማዕከላትን በማስፋፋት 1 ሺህ 567 ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የነዳጅ፣ የሲሚንቶ፣ የጨው እና ሌሎችም የግብይት ሥርዓት መዛነፍ የታየባቸውን መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እና ምርቶች በመመሪያ እና በአሠራር የማስተካከያ ርምጃዎችን በመውሰድ የዋጋ እና የአቅርቦት መረጋጋት እንዲፈጠር ማድረግ እንደተቻለም አስገንዝበዋል።
የሀገሪቱን የንግድ ሥርዓት ከአሕጉሩ እና ከዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት እና ሕግጋት ጋር ለማጣጣም አዳዲስ ደንቦችን፣ መመሪያዎች እና አሠራሮች ተዘጋጅተዋልም ብለዋል፡፡
ብሔራዊ የጥራት መንደር ንግድ እና ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ስምምነቶችን ለማስፈጸም የንግዱ ዓለም ልዩነት ፈጣሪ ቀለም መኾኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የጥራት መንደር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሕዳር 14/2017 ዓ.ም የተመረቀ በዓይነቱ ልዩ የኾነ የጥራት መሠረተ ልማቶችን የያዘ መኾኑን አስታውሰዋል።
ግዙፉ የጥራት መንደር ከተስማሚነት ምዘና እስከ ደረጃዎች ሥራ፣ ከአክሪዲቴሽን ክወና እስከ ሥነ-ልክ ትግበራ የሚሳለጥበት የዓለም የንግድ ልዩነት ፈጣሪ ቀለም መኾኑንም ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ታሪክ በበርካታ ዘርፎች ፋና ወጊ ድሎችን በማስመዝገብ ቀጣይነት ላለው ስኬት መሠረት ስለመጣሉም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት ከልማዳዊ አሠራር በማላቀቅ ከዘመናዊ የዓለም ንግድ አሠራር ጋር እንዲናበብ በማድረግ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ የንግድ አመቺነት እና ቀልጣፋነትን ለማረጋገጥ የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማገዝ ከ3 ሚሊዮን በላይ አገልግሎት በኦንላይን መስጠት ተችሏል ብለዋል።
የተሳለጠ እና እሴት የሚጨምሩ አሠራሮችን በመተግበር በ11 መስፈርቶች 32 ቀናት ይወስድ የነበረውን አሠራር ወደ ሦሥት መስፈርት እና ወደ ሰባት ቀናት ዝቅ ማድረግ ተችሏል፤ በቀጣይ ወደ አንድ መስፈርት እና አንድ ቀን ለማድረስ በትጋት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ከፍተኛ ለውጥ ከታየባቸው ዘርፎች መካከል የወጭ ንግድ ቀዳሚ መኾኑን በማንሳት በበጀት ዓመቱ ከወጭ ንግድ 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 161 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ባለብዙ ወገን ንግድ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ውጤታማ የትብብር እና ድርድር ተግባራትን እያከናወነች መኾኑንም ገልጸዋል።
በዚህም የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የዕቃዎች ቀረጥ ምጣኔ ቅነሳ ማስፈጸሚያ ደንብ መታተሙን እና ብሔራዊ የትግበራ ስትራቴጂ መጽደቁን ገልጸው ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የመጀመሪያ ጭነት ይጀመራል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሃመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“ትምህርት ለአንድ ሀገር ደም እና ስጋ ነው” ጋሽ አያልነህ ሙላቱ
Next article“የሀገር ውስጥ ምርትን መግዛት የኢኮኖሚ ዕድገትን የማሳለጥ ጉዳይ ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ