
አዲስ አበባ: ነሐሴ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ባንክ እና ቪዛ ኢትዮጵያ የዲጅታል ክፍያ ሥርዓትን ለማዘመን ተስማምተዋል።
ስምምነቱ ዓባይ ባንክ የኢትዮጵያን የዲጅታል ሽግግር ለማገዝ የሚያስችሉ የቪዛ አገልግሎቶችን እና ሌሎች ተግባራትን ለማስጀመር የሚያስችለው ይኾናል ተብሏል።
ስምምነቱ ዓባይ ባንክ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ምቹ እንዲሁም ዓለማቀፍ እውቅና ያላቸው የክፍያ መንገዶችን ለደንበኞች ለማቅረብ ያስችለዋል ተብሏል። የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በመቀነስ ባንኩ በዲጅታል የገንዘብ ዝውውር በስፋት እንዲሳተፍ የሚያግዝም እንደኾነም ተገልጿል።
የዓባይ ባንክ እና የቪዛ ዓለማቀፍ ስምምነት ባንኩ የዘመኑ ቴክኖሎጅዎችን እንዲጠቀም ያስችለዋል ነው የተባለው። የዓባይ ባንክ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ የኋላ ገሰሰ ባንኩ በሀገር ውስጥ 3 ሚሊዮን የዲጅታል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ተናግረዋል። ባንኩ ከቪዛ ኢንተርናሽናል ጋር ያካሄደው ስምምነት ዓለማቀፍ ክፍያዎችን የበለጠ ለማቀላጠፍ የሚያስችለው መኾኑንም ገልጸዋል። ደንበኞች በዓለማቀፍ ደረጃ ክፍያቸውን መፈጸም እንዲችሉ ከቪዛ ኢንተርናሽናል ጋር የተካሄደው ስምምነት ወሳኝ ነው ብለዋል። የቪዛ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪካ እና ቪዛ ኢትዮጵያ ኀላፊ ያሬድ እንዳለ ስምምነቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ዘመናዊ የዲጅታል አገልግሎትን ለመስጠት የተደረገ ስምምነት እንደኾነ ገልጸዋል። ዓባይ ባንክ እና ቪዛ ኢንተርናሽናል ያደረጉት ስምምነት ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ነው ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!