“አፍሪካውያን ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ልንከላከል ይገባል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

30
ባሕርዳር: ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀልን የመከላከል ቡድን ቀጣናዊ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባን አስጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አፍሪካውያን የሉዓላዊነታችን፣ የሀብታችንና የዕድገታችን ፀር የሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ልንከላከል ይገባል ብለዋል። 25ኛውን የምሥራቅ አወና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀልን የመከላከል ቡድን (ESAAMLG) ቀጣናዊ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባን ማስጀመራቸውንም ገልጸዋል። አፍሪካ በፍጥነት በሚለዋወጡ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በህገወጥ መንገድ የተገኘ የገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብ፣ ሽብርን በገንዘብ የመደገፍ እና በሌሎች ወንጀሎች እየተፈተነች ነው ብለዋል።
እነዚህ ወንጀሎች የዜጎቻችንን መሰረታዊ ጥቅሞች የሚነጥቁ፣ አህጉራዊ መሻታችንን የሚያሰናክሉ፣ እድገታችንን የሚያዳክሙና ድንበር ዘለል በመሆናቸው የትኛውም ሀገር ብቻውን ሊከላከላቸው አይችልም ነው ያሉት። እርምጃችን የወንጀሎችን ተለዋዋጭነት የሚመጥን፣ ጠንካራ፣ የተቀናጀ፣ በመረጃ ልውውጥና በትብብር ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል ብለዋል። ኢትዮጵያ ይህንን የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ፀር የሆነ አደጋ ለመከላከል ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁማ እየሠራች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝባችን፣ ከሌሎች ሀገራት እና ከአጋሮቻችን ጋር በመሆን ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleአሻጋሪ የልማት እቅዱ ቁጭትን የፈጠረ ተስፋን የሰነቀ ዕቅድ ነው።
Next articleየነዳጅ ግብይትን በቴክኖሎጂ አስደግፎ በመሥራት ሕገ ወጥ ድርጊቶችን መከላከል ይገባል።