የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማስገባት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ነው።

31
አዲስ አበባ: ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዳንጎቴ ግሩፕ የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት አድርገዋል።
የዩሪያ ማዳበሪያ ለማምረት የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት በዓመት ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ እንደሚያመርት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ገልጿል። የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ፕሮጀክቱ ሥራ ሲጀምር ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማስገባት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ሚናው የጎላ እንደሚኾን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶ እና የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የኑሮ መሠረት የኾነው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ውጤታማነቱን ከሚገዳደሩት ችግሮች አንዱ የግብዓት አቅርቦት እጥረት ነው።
ይህ ፕሮጀክት የግብዓት አቅርቦትን እጥረት ከመቅረፍ ባሻገር በቀጣይ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ያሳድጋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
ታላቅ ተስፋ የተጣለበት የዩሪያ ማዳበሪያ ፕሮጀክቱ በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ እንደሚገነባም ነው የተገለጸው። ፋብሪካውን ለመገንባትም 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጭ እንደሚደረግበት ነው የተገለጸው። ይህን ፋብሪካም ለመገንባት የኢትዮጵያ መንግሥት ከግዙፉ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ኩባንያ ”ዳንጎቴ ግሩፕ” ጋር ስምምነት አድርጓል። የኢትዮጵያን መንግሥት ወክለው ሰምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ብሩክ ታዬ (ዶ.ር) ፋብሪካው ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ 40 በመቶ እንዲኹም የዳንጎቴ ግሩፕ 60 በመቶ ድርሻ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል። ዋና ሥራ አሥኪያጁ ሲናገሩ የፕሮጀክቱ መገንባት ኢትዮጵያ ወደፊት ያላትን የተፈጥሮ ጋዝ ተጠቅማ የፔትሮ- ኬሚካል ኢንዱስትሪ ለመሥራት መሠረት ይጥላል ብለዋል።
በፊርማ ሥነ- ሥርዓቱ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ፋብሪካው ተጠናቅቆ ምርት ማምረት ሲጀምር ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማስገባት ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት። ይህ ሥራ ኢትዮጵያ የቀጣናው የማዳበሪያ አቅርቦት ማዕከል እንድትኾን እንደሚያስችላት አስገንዝበዋል። የዳንጎቴ ግሩፕ ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያደረጉት ስምምነት ታሪካዊ እና ትልቅ መኾኑን ገልጸው የፋብሪካው ዕውን መኾን የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላ አፍሪካም እንደሚያሳድግ ነው የገለጹት። የፕሮጀክቱ ግንባታ በ40 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የተገለጸ ሲኾን በዓመት ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የማምረት አቅም እንደሚኖረውም ተብራርቷል ። በስምምነት ሥነ ሥርዓቱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የዳንጎቴ ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ እና የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበተንቀሳቃሽ ማዕከላት የተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ምርመራ እየተሰጠ ነው።
Next articleመምህራን ተማሪዎች ተምረው ለቁም ነገር ሲደርሱ የሚሰማቸው ደስታ አንድ ገበሬ የዘራውን ሰብል ሲያጭድ የሚሰማው ስሜት ያክል ነው።