የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት መፈረሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ.ር) ገለጹ። 

24

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ወደ ምግብ ዋስትና እና የግብርና ሽግግር በምናደርገው ጉዞ አንድ ሌላ እጥፋት ላይ በመድረሳችን ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንኳን ደስ አለን ብለዋል።

 

ዛሬ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት ፈርመናል ነው ያሉት። 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት ይኽ ሜጋ ፕሮጀክት በዐቀመት እስከ ሦሥት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የሚያመርት ሲሆን ይኽም ኢትዮጵያን ከዓለም ግንባር ቀደም አምራቾች አንዷ ያደርጋታል ብለዋል።

 

ፕሮጀክቱ በሀገር ውስጥ የሥራ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት። ለዘመናት ለተፈተኑት ገበሬዎቻችን አስተማማኝ የማዳበሪያ አቅርቦት ያረጋግጣል። ለምግብ ሉዓላዊነት መንገዳችንም ወሳኝ ርምጃ መውሰዳችንን ያመላክታል። በመላው አኅጉሩ ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት በማጠናከር ሕዝባችንን እና ነጋችንን የሚጠቅሙ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን የመከወን ጽኑ አቋማችንን ያሳያል ብለዋል።

 

የዛሬውን የፊርማ ስምምነት ተከትሎ ፋብሪካው በሚቆምበት ስፍራ ፕሮጀክቱን በይፋ የምናስጀምር ይሆናል። ይኽን ታሪካዊ ጉዞ ጀምረናል። ለገበሬዎቻችን፣ ለኢኮኖሚያችን እና ለኢትዮጵያ ነገ ስንል እንጨርሰዋለን ነው ያሉት።

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየታጣቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።
Next articleፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ለመተማ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።