
አዲስ አበባ: ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ተቋሙ የሦሥት ዓመታት ስትራቴጂ እና የ2018 ጭቅዱን አስተዋውቋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተቋሙ ባለፉት ሦሥት ዓመታት በውጤት የተገበራቸው ሥራዎች ለሀገሪቱ ፈጣን እና የለውጥ ጉዞ ትልቅ አበርክቶ እንደነበራቸው ገልጸዋል።
ከ2018 እስከ 2020 ድረስ የሚዘልቀው የተቋሙ የሦሥት ዓመት ስትራቴጂ እቅድ “ቀጣዩ አድማስ”የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ስትራቴጂው የወጡ ሕግ እና ፖሊሲዎችን መሠረት አድርጎ የፋይናንስ፣ ዲጂታል አካታችነትን እና ሰው ተኮር ሥራዎችን በውስጡ የያዘ ነው ብለዋል።
አትዮ ቴሌኮም ተወዳዳሪ እና ችግር ፈቺ የኾኑ አዳዲስ እሳቤዎችን ይዞ ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ የቴሌኮም ዘርፎች ለመቀላቀል ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች ተጠቅሞ ዝግጅት ማድረጉንም አመላክተዋል።
በስትራቴጂው ከሁሉም አቅጣጫ ያሉ ስጋቶችን በመተንበይ የደንበኞች ደኅንነት እንዲጠበቅ እና አስተማማኝ አገልግሎትን ለመስጠት ማቀዱንም ገልጸዋል። ለእቅዱ መሳካት ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት እቅዱ አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት በአስር ከተሞች ተጨማሪ የአምስተኛው ትውልድ (5G) አገልግሎትን በመዘርጋት የሞባይል ኔትወርክ ሽፋን ለማሳደግ እንደሚሠራ ተገልጿል። ተቋሙ የደንበኞቹን ቁጥር አሁን ካለው 83 ሚሊዮን ወደ 88 ሚሊዮን በማድረስ 235 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱም ተመላክቷል።
በሦሥት ዓመት ስትራቴጂ “የቀጣይ አድማስ” እቅዱ ደግሞ የደንበኞቹን ቁጥር 100 ሚሊዮን በማድረስ 842 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱ ነው የተገለጸው።
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን