
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የ30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የማጠቃለያ ዝግጅት እየተካሄደ ነው።
በማጠቃለያ ዝግጅቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የርእሰ መሥተዳድሩ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ እና የአሚኮ የሥራ አመራር ቦርድ ሠብሣቢ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። በማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ የአሚኮን የ30 ዓመታት የምሥረታ በዓል ማክበር ያሰብነው ትናንት የሠራነውን ለመዘከር ብቻ ሳይኾን ለነገም መሠረት ለመጣል ነው ብለዋል። አሚኮ በጋዜጣ ጀምሮ ታላቅ የኾነ የራሱ መልክ ያለው ነው ብለዋል። የአሚኮ 30 ዓመታትን ለማክበር ያሰብነው ቤተሰባዊነትን እና አንድነትን ለማጠናከር ነው ያሉት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው አሚኮ ብዝኀ ልሳን፣ ብዝኀ ሕዝብ፣ ብዝኀ ድምጽ እንደኾነም ገልጸዋል።
አሚኮ ለሕዝብ ዋጋ እየከፈለ የሚሠራ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል። አሚኮ የሚዘግበው ለሕዝብ ፋይዳ ያለውን ጉዳይ ተረድቶ መኾኑንም ተናግረዋል። አሚኮ በችግር ውስጥ የሚሠራ፣ ችግሮችን የሚያልፍ መኾኑንም ገልጸዋል። ለመጭው ዘመን ከሚኖረው ችግር በላይ ለመሥራት እና ከችግሮች ለማሻገር ዝግጅት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። አሚኮ ሀገር ችግር ውስጥ ስትገባ ከችግር ለማውጣት የሚሠራ እና ከችግር በላይ የሚያስብ መኾኑንም ተናግረዋል። በማጠቃለያ ዝግጅቱ ለአሚኮ አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማት እና ድሮጅቶች ዕውቅና እንደሚሠጥም ገልጸዋል።
አሚኮ ጥራት እና ፍጥነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ሁሉን አቀፍ የለውጥ ሥራ ላይ መኾኑንም አንስተዋል። አሚኮ ራሱን በቴክኖሎጂ እያዳበረ፣ ተደራሽነቱን እያሰፋ እንደሚሄድም ገልጸዋል። የአማራ ክልል የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ እንዲሳካ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዲከበር፣ አብሮነት እንዲጠናከር እንደሚሠራም አንስተዋል። አሚኮ እዚህ እንዲደርስ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል። የአሚኮ አዲሱ ምዕራፍ ወደ ልህቀት የሚሸጋገርበት እንደኾነም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን