
ባሕር ዳር: ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አያሌ ፈተናዎች ደርሰውበታል። የበዙ ችግሮች ተደራርበውበታል። ወጀቦችም አይለውበታል። በግራና በቀኝ፣ በፊት እና በኋላ የሚወረወሩ ጦሮች በርክተውበታል።
ነገር ግን ሁሉንም በጽናት ተሻግሯቸዋል። ፈተናዎችን በጥበብ አልፏቸዋል። ችግሮችን በብልሃት ፈትቷቸዋል። ወጀቦችንም በጽናት መክቷቸዋል።
ረጅሙን ጉዞ በጥቂት ዓመታት ተጉዞታል። በዕድሜ የሚቀድሙት፣ እርሱ ገና ዳዴ በሚልበት ዘመን ታላቅ የነበሩት ያልደረሱበትን ደርሶበታል። ቀደምቶቹ ያልተሻገሩትን ተሻግሮታል። ቀደምቶቹ ያልነኩትን ነክቶታል፤ ቀደምቶቹ ያላሳኩትን ስኬት አሳክቶታል። አሁን ላይ የሚሊዮኖችን ልብ በአዎንታ ገዝቶ በልባቸው ዙፋን ላይ ተቀምጧል፤ ችግራቸውን ያዋዩበታል። ብሶታቸውን ይነግሩበታል፤ ተስፋቸውን ይገልጹበታል። መሻታቸውን ያወጡበታል። ደስታቸውንም ያካፍሉታል።
መፍትሔ በጠፋ ጊዜ መፍትሔ ያዩበታል። እውነትን ያገኙበታል። ሕይወታቸውን በመልካም ይመሩበታል። በሩቅ ያሉት ናፍቆታቸውን ይወጡበታል። የሀገራቸውን እና የሕዝባቸውን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ይመለከቱበታል። ሚዛናዊ የኾነውን ሃሳብ ያገኙበታል። ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅመውን ሃሳብ ይረዱበታል አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን አብዝቶ በሚወድ ሕዝብ መካከል ተመሥርቷል። ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በትጋት ሠርቷል። የኢትዮጵያን ክብር አጉልቷል። ኢትዮጵያዊነትን እና አንድነትን በሥራው አደርጅቷል። የጠለቀ ባሕል እና እሴት፣ ታሪክ እና ሃይማኖት ባለው ሕዝብ መካከል ተመሥርቷልና ለባሕል እና እሴት፣ ለታሪክ እና ሃይማኖት መጠበቅ ሠርቷል። ያልታየውን አሳይቷል፤ ያልተሰማውን አሰምቷል። የተሰማውን አጉልቷል፤ የተዳፈነውን ገልጧል። የተዳከመውን አጠንክሯል።
ዕድሜው ገና ሠላሳ ዓመት ወጣት ነው። ሥራው ግን ከዚያም ያለፈ እና የገዘፈ ነው።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ አሚኮ የብዙኃን ነው፤ ለብዙኃን ጥቅም ዋጋ እየከፈለ የሚሠራ፣ ብዙኃን የሚናገሩበት ነው ይሉታል። አሚኮ የተሻገራቸው ምዕራፎች አሉት የሚሉት ሥራ አሥፈጻሚው አስቀድሞ ገና በአማራ ክልል ሚዲያን ካለመኖር ወደ መኖር አመጣ። ወሳኙ ምዕራፍም ካለመኖር ወደ መኖር የመጣበት ነበር። በበኩር የበኩርና ሥራውን የጀመረው አሚኮ በሁሉም የሚዲያው ታሪክ ከመኖር ወደ አለመኖር የመጣበት ምዕራፍ ቀዳሚው ነው ይሉታል። በጋዜጣ ጀምሮ በሬዲዮ ተከትሎ፣ በቴሌቪዥን የሰለሰው አሚኮ አሁን ላይ በብዙ ቋንቋዎች እና የሚዲያ አማራጮች እየሠራ ነው። አሚኮ ካለመኖር ወደ መኖር ከመጣ በኋላ ይዘትን መቅረጽ፣ ሙያዊ ማድረግ፣ ሚዲያውን የሚዲያ ቅርጽ መስጠት ደግሞ ሁለተኛው ምዕራፍ ነው ይላሉ። በሁለተኛው ምዕራፍ አሚኮ የራሱን ቀለም የያዘበት ነው። አሚኮ ሁሉም የሚናገሩበት፣ ሁሉም የሚገለገሉበት የሁሉም ነው ብለዋል ሥራ አስፈጻሚው።
የዲጂታል ሚዲያው የመጣበት ደግሞ የአሚኮ ሦሥተኛው ምዕራፍ ነው። የዲጂታል ሚዲያ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ የመጣ፣ ሌሎች ሚዲዬሞችን ያዋሐደ፣ አንድ ያደረገ ነው ብለውታል። የዲጂታል ሚዲያው ዕድገት ቀጣይነት ያለውም ነው ይላሉ። አሚኮ በጋዜጣ፣ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን የራሱን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ሁሉ በዲጂታል ሚዲያውም የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን ገልጸዋል። ዲጂታል ሚዲያውን ከዚህ በላይ ካሳደግነው ደግሞ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ በውጭ የተወለዱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባሕል እና ወግ እንዲያውቁ ያደርጋል ነው የሚሉት። አሚኮ መነሻው እና ሃብትነቱ የአማራ ክልል ሕዝብ ይሁን እንጂ መዳራሻው እና አገልግሎቱ ግን ለመላው ኢትዮጵያውያን እና ከዚያ ባሻገር ነው ይላሉ። የአማራ ክልል ሕዝብን መብትና ጥቅም ለማስከበር፣ እሴቱን ለማጠንከር፣ ገጽታውን ለማሳደግ ይሠራል ነው ያሉት።
አሚኮ በመላው ኢትዮጵያ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ሰላም እንዲፈጠር ይሠራል። አሚኮ ለኢትዮጵያውያን የቆመ ስለኾነ በአሥራ ሁለት ቋንቋቸው አገልግሎት እየሰጠ ነው። ሚዲያ የአንድን ሀገር ሕዝብ በሥነ- ልቦና አስተሳስሮ ይኖራል ያሉት ሥራ አሥፈጻሚው አሚኮም ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር እየሠራ መጥቷል፤ ይሠራልም ብለዋል። አሚኮ በሠላሣ ዓመታት ጉዞው ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምጽ ኾኗል። የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የሕጻናት እና የአረጋውያን መብት እንዲከበር ታትሯል። ይህም የብዙኃን ድምፅ እና ብዙኃን የሚናገሩበት መኾኑን ያሳያል ነው የሚሉት።
የአሚኮ ሠላሣኛ ዓመትን ስናከብርም የሠላሣ ዓመታትን ጉዞ እናስባለን የሚሉት ሥራ አሥፈጻሚው ጋዜጠኛ መሉቀን የሠላሣ ዓመታት ጉዞው ቀላል አይደለም፣ ካለመኖር ወደ መኖር ከመምጣት ተነስቶ ትልቅ ተቋም ኾኗልና ነው ያሉት። በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት እንደ አሚኮ መሪዎች እና ሠራተኞች የተፈተነ የለም፣ ያን ሁሉ ፈተና ያለፉ መሪዎች እና ሠራተኞች አሉት። የአሚኮ የሠላሣ ዓመታት ጉዞን ስናስብ በፈተና ውስጥ የጸኑ መሪዎች እና ሠራተኞች ዕውቅና እንሠጣለን፣ የውስጥ አንድነትን እናጠናክራለን፣ ለቀጣይ ስንቅ የሚኾን ጉዳይ እንይዛለን ብለዋል። አሚኮን ማስተዋወቅ ሌላኛው የበዓሉ ዓላማ መኾኑን ነው ያነሱት። ጠንካራ አሚኮን እንፈጥራለን፣ ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር ያለንን ግንኙነት እናጠናክራለን በማለት ጨምረዋል።
በዓል ብቻ አናከብርም የሚሉት ሥራ አሥፈጻሚው ለቀጣይ ሠላሣ ዓመታትም መሠረት እንጥላለን። በጊዜው እና በወቅቱ መጀመር የሚገባቸውን እንጀምራለን ይላሉ። ባለፉት ዓመታት ለሚዲያ ሥራ ፈታኝ ጊዜ ነበር። ነገር ግን በፈተና ውስጥ በርካታ ሥራዎችን ሠርተናል። አሁንም በችግር ሳንቆም ለቀጣይ መሠረት የሚኾን ሥራ እንሠራለን ነው ያሉት። አሚኮ ለሰው ኀይል ልማት በሰጠው ትኩረት ታላላቅ የሚዲያ መሪዎች እና ጋዜጠኞች ከአሚኮ ወጥተዋል፣ በዚህ ደግሞ እንኮራለን፣ በቀጣይም ለሰው ሃብት ልማት ትኩረት እንሰጣለን ብለዋል። ቴክኖሎጂን ማዘመን፣ ዲጂታላይዜሽንን መተግበር የአሚኮ የቀጣይ የትኩረት መስክ መኾኑንም ገልጸዋል። ቴክኖሎጂ ሲያድድግ ይዘት ያድጋል፣ ይዘት ሲያድግ ደግሞ የውስጥ ገቢ ያድጋል፣ የውስጥ ገቢ ሲያድግ ደግሞ ሚዲያው በሁሉም መልኩ ያድጋል ይላሉ።
ኢትዮጵያ መቸገር አይመጥናትም፣ ኢትዮጵያ እንድታድግ ደግሞ ጋዜጠኞች አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው ያሉት አቶ ሙሉቀን አሚኮም ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጉን ይቀጥላል ብለዋል። አሚኮ ጥሩ ዕድገት ላይ ነው፣ ነገር ግን ከዚህም በላይ ማሳደግ አለብን፣ ለሚዲያ ፈታኝ በኾነ ጊዜ ውስጥ ጥሩ ሥራዎችን ሠርተናል፣ ፈተናዎቹ ሰበብ መኾን ይችሉ ነበር፣ ነገር ግን ሰበብ መፍጠር አልፈልግንም፣ በትኩረት ተሠርቷል፣ የሥራ አመራር ቦርዱ፣ ምክር ቤቱ፣ የክልሉ መንግሥት እገዛ እና ትኩረት ታላቅ ነበር ነው ያሉት። አሚኮ አሁን ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከኾኑ ጥቂት የኢትዮጵያ ሚዲያዎች መካከል አንደኛው ነው። ነገር ግን የቀደመ ሥልጣኔ፣ ታላቅ ታሪክ፣ የራሱ የኾነ የዘመን ቀመር ላለው ሕዝብ ከዚህም በላይ ያደገ ሚዲያ ያስፈልገዋል፤ ለዚህ ደግሞ በአንድነት እና በቁርጠኝነት መሥራት ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ጠንካራ ሚዲያ ሲኖር ሰነፍ ተቋማት አይኖሩም፤ ተቋማት በሚዲያ እንዳይጋለጡ በጥንካሬ ይሠራሉ። ስለዚህ ጠንካራ ሚዲያ እንዲኾን ይፈለጋል ነው ብለዋል።
አሚኮ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ በትኩረት ይሠራል። የተመሠረተበት ሕዝብም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እንዲጸና መስዋዕትነት ሲከፍል የኖረ ነው። በዚህ ሕዝብ መካከል የተመሠረተ ተቋም ደግሞ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የመሥራት ኀላፊነት አለበት በማለት አስረግጠዋል። አሚኮ በሠላሣ ዓመታት አያሌ ሥራዎችን ሠርቷል። ከዘመኑ የቀደመ ጉዞውም ተጉዟል። አሁንም ጉዞውን በትጋት ይቀጥላል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የደመቀ ታሪክ ያኖራል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!