ሚዲያዎች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ሞግተው መቆም አለባቸው። 

16

ባሕር ዳር: ነሐስ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የ30ኛ ዓመታት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ አውደ ጥናት ተካሂዷል።

 

የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች አሚኮ ለሀገር ሰላም እና ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ የመጣ ተቋም መኾኑን ገልጸዋል። አሚኮ የራሱን ሥርዓት የገነባ ዘመናዊ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል። አሚኮ አሁን ካለበት በላይ እንዲያድግ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባም ተናግረዋል።

 

ሀገር ሰላም እንድትሆን፣ አንድነት እንዲጠናከር የሚዲያዎች ሚና የላቀ መኾኑንም አንስተዋል።

ማኅበራዊ ኀላፊነት ያላባቸው ሚዲያዎች ግጭትን የሚያባብሱ ሃሳቦች እንዲረግቡ፣ ሀሰተኛ መረጃዎች እንዲመክኑ ሚናቸው የላቀ መኾኑንም አንስተዋል። ሚዲያዎች ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥ መሥራት እንደሚገባቸውም አንስተዋል።

 

“የቀውስ ወቅት እና የሚዲያ ሚና” በሚል ርእሰ ጥናት ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን መምህር እና ተመራማሪ ጀማል መሐመድ (ዶ.ር) አጀንዳችን የሚለካ እና ግብ የሚመታ መኾኑ አለበት ብለዋል። አጀንዳው ግብ እንዲመታ ማጥናት፣ አቀራረብን ማዘመን እና በተደጋጋሚ ማስረጽ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

 

ሚዲያዎች ግጭትን በሚያረግብ እና ሰላምን በሚያረጋግጥ መልኩ መረጃዎችን ማድረስ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ሚዲያዎች ግጭትን ሲያረግቡ ግጭትን እንደሚያስቀሩ ነው የገለጹት።

 

የጋዜጠኝነት ሙያን ማዳበር እና ሙያን በአግባቡ ማሳደግ እንደሚገባም አመላክተዋል። የሚዲያ አጠቃቀም ዕውቀትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

 

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ አሚኮ በይዘት መረጣ እና በሌሎች ሥራዎቹ ተመራጭ ሚዲያ መኾኑን ገልጸዋል። ሀገራዊ ጉዳዮችን በትኩረት የሚሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። አሚኮ ባለፉት ዓመታት በፈተና ውስጥ ኾኖ ውጤታማ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል።

 

ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ እና ለመሪያቸው ጥሪ ምላሽ እየሰጡ ዋጋ ሲከፍሉ ኖረዋል ያሉት ሚኒስትር ድኤታው ኢትዮጵያውያን ለብሔራዊ ጥቅም ጥሪ ያላቸውን ቀናዒነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚዲያዎች በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

 

ለብሔራዊ ጥቅም መረጋገጥ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሚኒስትር ድኤታው ቀውስን ለማርገብ እና ሰላምን ለማረጋገጥ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።

 

“ብሔራዊ ጥቅም እና የሚደያ ሚና” በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ.ር) ብሔራዊ ጥቅም የአንድ ዜጋ የመጨረሻ እና ቀሪ ሀብቱ ነው ብለዋል። የአንድ ዜጋ የመጨረሻ ሃብቱ ቤት እና ንብረቱ ሳይኾኑ ሀገሩ ናት ነው ያሉት። የሀገር ጉዳይ የመጨረሻ ሃብቴ ነው የሚል የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ተቋም ከተፈጠረ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ እንደሚቻል አንስተዋል።

 

ሚዲያዎች ብሔራዊ ጥቅም ከሁሉም በላይ የኾነ መኾኑን ማስረጽ እንደሚገባቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ ሌሎች ጉዳዮች እና ጥያቄዎች ብሔራዊ ጥቅምን እንዳይጋፉ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን ነው ያሉት። የትኛውም ሚዲያ በብሔራዊ ጥቅም እና በብሔራዊ አጀንዳ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል።

 

ስኬቶችን ከሀገር አጀንዳ እና ከብሔራዊ ጥቅም ጋር ማያያዝ እና በዚያ መልኩ መለካት እንደሚገባም አመላክተዋል። የኢትዮጵያን ክብር እና ልዕልና በሚያስከብሩ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።

 

አሚኮ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የተናገሩት ሚኒስትሩ ይሄን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟ ከተረጋገጠ እና ከበለጸገች ሁላችንም ያልፍልናል፣ እርሷ ከተጎዳች ግን ሁላችንም ተጎጅዎች ነን ብለዋል።

 

ሚዲያዎች የውስጥ አቅም እንዲያድግ፣ ሕገ ወጥ አሠራሮች እንዲታረሙ ማድረግ እንሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምን በሚገባ ተረድቶ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ የብሔራዊ ጥቆሞቿ እንዲረጋገጡ መሥራት ከሚዲያዎች የሚጠበቅ ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል።

 

የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤ ሚዲያ ለሀገር ዕድገት ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸዋል። የአማራ ክልል መንግሥት አሚኮ እንዲያድግ እየሠራ ነው፣ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

 

ሚዲያዎች በቀውስ ጊዜ መረጃን ቀድመው መስጠት፣ መረጃውን ሚዛናዊ እና የተማከለ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ቀውሱ እንዲረግብ እና እንዲፈታ የመፍትሔ ሃሳብ ማመላከት እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል። የየትኛውም ሀገር ሚዲያ ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ይሠራል ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤው የእኛ ሀገር ሚዲያዎችም ለሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም ሞግተው መቆም አለባቸው ነው ያሉት።

 

ሚዲያ ሀገርን እንዳያፈርስ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። ሕዝብ ለአንድነት፣ ለልማት እና ለእድገት በቁጭት እንዲነሳሳ መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በሕዝብ መካከል የጋራ ትርክት፣ የጋራ ትውስታ እንዲኖር መሥራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። የጋራ ርዕዮችን እንዲጠናከሩ መሥራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

 

ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሳኩትን ድል ማጉላት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ምክትል አፈ ጉባኤው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጥያቄ የትውልዱ አጀንዳ መኾኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መብቷ እንዲረጋገጥ እና ተጠቃሚ እንድትሆን ሚዲያዎች በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

 

ለሀገራዊ ሰላም እና ደኅንነት መሥራት እንደሚጠበቅም አንስተዋል። ሕዝብን ለዘመናት ከጎዱት የግጭት እና የድህነት አዙሪት እንዲወጣ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። የሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲኾን እና የጋራ መግባባት እንዲፈጠር መሥራት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

 

አሚኮ በአጭር ጊዜ ፈጣን እድገት ያሳየ፣ የችግሮች ወጀብ ሳያናውጠው ለሀገር ጥቅም እና ሰላም መሥራቱን ተናግረዋል። አሚኮ በወጀብ ሳይናወጥ እና ሳይገፋ በጽናት ለሠራው ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ እና በክልሉ ምክር ቤት ዕውቅና እንደተሰጠው አንስተዋል።

 

አሚኮ ፈተናዎች ሊገጥሙት እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ በትኩረት እንዲሠራም አሳስበዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲፈታ፣ የውይይት ባሕል እንዲያድግ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። አሚኮ በሚሠራው ሥራ ሁሉ የክልሉ ምክር ቤት እና መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

 

በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአሚኮ ዕድገት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

 

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

 

ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበገንዳውኃ ከተማ የ2018 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ተጀምሯል።
Next articleአሚኮ እዚህ ለመድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል።