“በሁሉም መስክ የተሻለች አፍሪካን ለመገንባት ለትምህርት ጥራት ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

31
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 41ኛውን የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ዓመታዊ ጉባኤን ከፍተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ትምህርት የአፍሪካን የለውጥና የመነሳት ጉዞ እንዲመራ ለአንድ ዓላማ በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል። ዛሬ ኢትዮጵያ እያስተናገደች ያለውን 41ኛውን የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ዓመታዊ ጉባኤን ከፍተናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካ እያደገች ነው፤ ነገር ግን ይህ በቂ አይደለም የመጪው ዘመን መሪ ልትሆን ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ ልጆች የመማር እድልን ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ፣ ተገቢ እና ጥራት ያለው ትምህርት ማግኘታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ አንስተዋል።
የትምህርት ምዘና መማርን የምንለካበት ብቻ ሳይሆን ያለንበትን የሚነግረንና ወደየት መሄድ እንዳለብን የሚመራን ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የትምህርትና የምዘና ስርዓቷ ፍትሐዊ፣ ትርጉም ያለው እና በንድፈ ሀሳብ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን በተግባራዊ ክህሎቶች ላይ ያተኮረ እንዲሆን ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው መኾኗን ገልጸዋል። በሁሉም መስክ የተሻለች አፍሪካን ለመገንባት ለትምህርት ጥራት ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል። ለዚህም አህጉራዊ አንድነትን የሚያጠናክር፣ ባሕላዊ ዕውቀትን የሚያከብር፣ አፍሪካዊ ዕውቀትን መቅሰም የሚያስችል የጋራ አህጉራዊ የትምህርትና የምዘና ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleበየዘርፉ ለአሚኮ እየተሰጡ ያሉ ዕውቅናዎች የኮርፖሬሽኑ የላቀ አፈፃፀም ብቃት ማሳያዎች ናቸው።
Next article“ለግጭት ያበቃን አለመወያየት ነው” ጀማል መሐመድ (ዶ.ር)