“አሚኮ የማይቻሉ የሚመስሉ ፈተናዎችን አልፎ ለስኬት የበቃ ተቋም ነው” ምክትል አፈጉባኤ አማረ ሰጤ

14
ባሕር ዳር: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) የ30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ዐውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።
በዐውደ ጥናቱ ማስጀመሪያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ሰጥዬ አሚኮ በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ሁለተኛ በኾነችው በኩር ጋዜጣ ሥራውን መጀመሩን ገልጸዋል። አሚኮ ቀስ በቀስ እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል። በክልሎች ታሪክ የመጀመሪያ ኾኖ የጀመረው አሚኮ አሁን ላይ ታላቅ ተቋም መኾኑን አንስተዋል። በአንድ ጋዜጣ የጀመረው አሚኮ አሁን አራት ጋዜጦች፣ ሰባት የሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና በርካታ የዲጂታል ሚዲያ አማራጮች እንዳሉት ገልጸዋል። የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች ለሕዝብ እየደረሰ እንደሚገኝም ተናግረዋል። አሚኮ ሕዝብ የሚናገርበት እና የሃሳብ ነጻነትን የሚያበረታታ ተቋም ነው ብለዋል። ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ሚዲያዎች እንደ አሚኮ የተፈተነ እና በፈተና ውስጥ ያለፈ ሚዲያ እንደሌለም ገልጸዋል።
አሚኮ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲፈታ፣ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ የሠለጠነ ፖለቲካ እንዲኖር በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
አሚኮ ዕውቀት እና መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ በስፋት ሢሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል። የዛሬው ዐውደ ጥናትም የዚሁ አንድ አካል ነው ብለዋል።አሚኮ ልሂቃን በሃሳብ እየተከራከሩ ሕዝብ የሚጠቅመውን ሃሳብ እንዲወስድ ይሠራልም ብለዋል። ሚዲያ ለብሔራዊ ጠቅም እና ለሀገር ሰላም አስተዋጽኦው ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው አሚኮ ብሔራዊ ጥቅም እንዲከበር፣ ሰላም እንዲረጋገጥ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ አሚኮ የማይቻሉ የሚመስሉ ፈተናዎችን አልፎ ለስኬት የበቃ ተቋም ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል እና በመላው ኢትዮጵያ ልማት እንዲስፋፋ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦ ያደረገ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል።
የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲቀለበስ ያደረገ ተቋም መኾኑንም አንስተዋል። የሚዲያ ተደራሽነት እንዲሰፋ ያደረገ፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመረ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል። አሚኮ ከዚህ የበለጠ እንዲያድግ እና እንዲጠናከር ሁሉም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአሚኮን 30ኛ ዓመታት የምሥረታ በዓል አስመልክቶ የተዘጋጀው አውደ ርዕይ ተከፈተ።
Next articleከክረምቱ ጋር ተያይዞ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ልዩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።