
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከ1000 ሕጻናት መካከል አንድ ሕጻን በተፈጥሮ ቆልማማ እግር ኖሮት ይወለዳል ይላል። በየዓመቱ እስከ 200 ሺህ ሕጻናት ቆልማማ እግር ኖሯቸው እንደሚወለዱም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት::
80 በመቶው የሚኾኑት ደግሞ በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባለቸው ድሀ ሀገራት የሚገኙ ናቸው ይላሉ በደብረ ብርሃን ከተማ የሐኪም ግዛው መታሠቢያ ሆስፒታል የአጥንት እና መገጣጠሚያ ስፔሻሊስት ዶክተር ብስራት ጥላዬ። በሀገራችን ኢትዮጵያ በተሠራ አንድ ጥናት ደግሞ ይህ አሃዝ ከፍ ይላል። ከአንድ ሺህ ሕጻነት ከሰባት በላይ የሚኾኑት ቆልማማ እግር ኖሯቸው እንደሚወለዱ ያሳያል። የችግሩ መነሻ ምክንያት በውል ባይታወቅም በሕክምና የሚስተካከል ችግር መኾኑን ግን ማኅበረሠቡ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል ዶክተር ብስራት። የፈጣሪ ቁጣ ነው በሚል የተሳሳተ አመለካከት የችግሩ ተጋላጭ ሕጻናትን በመደበቅ ለሌሎች ውስብስብ ችግሮች መዳረግ እንደማይገባም ገልጸዋል።
የጀሶ ህክምና ችግሩን ለማስተካካል ወርቃማው የህክምና አማራጭ ስለመኾኑም ዶክተሩ ተናግረዋል። የጀሶ ህክምና ከ95 በመቶ በላይ ውጤታማ እንደኾነም ገልጸዋል። መለስተኛ የጅማት ቀዶ ሕክምናና የድጋፍ ጫማም የችግሩ የሕክምና አማራጮች ናቸው ነው ያሉት። በደብረ ብርሃን ሐኪም ግዛው መታሠቢያ ሆስፒታል ሕክምናው በነጻ እንደሚሰጥ የገለጹት ዶክተር ብስራት የዚህ ችግር ተጋላጭ የኾነ ልጅ ያላቸው ወላጆች ወደ ሕክምና ተቋም በመውሰድ በቀላሉ በህክምናው ተጠቃሚ በመኾን የችግሩን ተጋላጮች ከአካል ጉዳተኝነት ሊታደጉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን