ቴክኖሎጂን በውጤታማነት መጠቀም ዘመኑ የሚጠይቀው ብልህነት ነው።

43
ባሕር ዳር: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “በዲጂታል ዕውቀት እና ክህሎት የታነፀ ትውልድ ለአሻጋሪ እና ዘላቂ ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት የዲጂታል አማራ ኢኒሼቲቭ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የዲጂታሉ ዓለም እጅግ ፈጣን በኾነ የዕድገት ግስጋሴ ላይ ነው ብለዋል። የሰዎችን የዕለት ከዕለት ተግባራት ከማቃለል ጀምሮ ትልልቅ እና ውስብስብ ሥራዎችን በፍጥነት እስከመከወን ድረስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የዘርፉ አዳዲስ ግኝቶች በተገልጋዮች በኩል ሰፊ ተቀባይነት በማግኘታቸው እና ከዚህ ቀደም ከተለመደው በተለየ መልኩ ወደ ሕዝቡ ገብተው በፍጥነት ሲሰርጹ ይታያሉ ነው ያሉት። የዲጂታል ቴክኖሎጂውን ባሕሪ ቀድመው የተረዱ ሀገራት ዜጎች ዕድሉን በመጠቀማቸው ከፊት መቅደማቸውን ገልጸዋል። ቴክኖሎጂ የትምህርት ሥራውን በሚያሳልጥ፤ የልጆችን አስተሳሰብ በሚያጎለብት መልኩ በአግባቡ እና በውጤታማነት መጠቀም ዘመኑ የሚጠይቀው ብልህነት ነው ብለዋል። መምህራን ዘመኑን የሚዋጅ ዕውቀት እና ክህሎት የተላበሰ ትውልድ ለመፍጠር እራስን ከዘመኑ ጋር ማላመድ ግድ መኾኑን ማወቅ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
መምህራን ለዚህ ዝግጁ እንዲኾኑ መደገፍ የዚህ ፕሮግራም አንዱ ተግባር ይኾናል ብለዋል። የትምህርት ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት መስጠት ልጆቹ መረጃ በፍጥነት እንዲያገኙ፣ የመማር ማስተማር ሥራው ሳቢ እና ማራኪ እንዲኾን እንደሚያደርግ እና አጠቃላይ ዕውቀትን ያሳድጋል ነው ያሉት። ዘመኑ ጋር የተግባቡ ዜጎችን ለመፍጠር እንደሚያስችልም ተናግረዋል። ዜጎች የዲጂታል ዕውቀታቸው እንዲጎለብት እና ክህሎታቸው ዳብሮ በዓለም አቀፍ ገበያው ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ማድረግ ጊዜው የሚያስገድድ እና የሁሉንም ስፊ ርብርብ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ዲጂታል ኢኒሸቲቮችን ሥራ ላይ ለማዋል አገልግሎቶችን ዲጂታይዝ የማድረግ እና ከስው ንክኪ ነጻ የኾኑ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ትውልዱን በዲጂታል ዕውቀት እና ክህሎት ከታች ጀምሮ አንጾ ማውጣት ለነገ ማይባል ተግባር ነው ብለዋል። የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ ትምህርትን ተጨባጭ እና ዕውነተኛውን ዓለም እንዲመስል ለማድረግ ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ነው የተናገሩት። የተቀናጀ እና የተሰናስለ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ለመስጠት ዘመናዊ የመሳሪያ ክፍል ማደራጀት፣ የኢንተርፕርነርሽፕ እና የቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ማዕከል በማቋቋም ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና መስጠት ብሎም የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ ክህሎት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በሂደትም የዲጂታል ትምህርት ተደራሽነት አድማሱን በማስፋት በክልሉ የሚገኙ ዜጎችን በዲጂታል ዕውቀት ማዘጋጀት፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ልማት ውስጥ የላቀ ሚና እንዲኖራቸው ማስቻል ግድ ይላል ነው ያሉት። ተማሪዎች በዲጂታል የሥራ ዓለም ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲኾኑ ለማስቻል እየተሠራ ነው ብለዋል። በደረጃቸው ሥራ ፈጣሪ እና በቴክኖሎጂው ተጠቃሚ የሚኾኑ ተማሪዎችን ለማፍራት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጅ (አይቲ) ትምህርትን የበለጠ ገቢራዊ እንዲኾኑ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ዲጂታልን በውጤታማነት ለመተግበር የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
በአፍሪካ ልማት ማዕከል የአማራ ክልል የቅድመ ልጅነት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢኒሼቲቭ አስተባባሪ አየልኝ ሙሉዓለም የዲጂታል አማራ ዋና ግብ ዜጎችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረግ እና የኢኮኖሚው ተሳታፊ እንዲኾኑ ማዘጋጀት ነው ብለዋል። የ21ኛው ክፍለ ዘመን ቴክኖሎጂ ላይ መሠረት ያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል። ዜጎችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ወጣቶችን ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢኮኖሚ ማዘጋጀት ግድ እንደሚልም አስታውቀዋል። የክልሉን ትምህርት በዲጂታል መደገፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleአሚኮ በመሰዋዕትነት ውስጥ እያለፈ ሀገር ያጸና ሚዲያ ነው።
Next articleበገንዳ ውኃ ከተማ የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር ተካሄደ።