
ባሕር ዳር: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “በዲጂታል ዕውቀት እና ክህሎት የታነፀ ትውልድ ለአሻጋሪ እና ዘላቂ ዕድገት” በሚል መሪ መልዕክት የዲጂታል አማራ ኢኒሼቲቭ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኀላፊ አቤል ፈለቀ በቴክኖሎጂ መዘመን እና መስፋፋት ምክንያት የዕውቀት ምንጮች ላይ ትልቅ ለውጥ ፈጥሯል ብለዋል። በበይነ መረብ እና በሳይበር ምህዳር ምክንያት የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ላይ ሁለት መልክ ያላቸው ዕድሎች እና ለውጦች ተከስተዋል ነው ያሉት። ሃርድ ኮፒ ብዜት ላይ መሠረት ያደርጉ የነበሩ የትምህርት መሳሪያዎችን በቀላሉ፣ በነጻ እና በተለያዩ የይዘት አማራጮች ያለ ቦታ እና ጊዜ ገደብ ተደራሽ እንዲኾኑ ማድረጉ የመጀመሪያው እና በጎ አማራጭ ነው ብለዋል።
የትምህርት ተደራሽነት በጥራት እና ወጥ በኾነ መልኩ ለማረጋገጥ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ማስፋት እና ኤሌከትሮኒክስ መሳሪያዎችን ማቅረብ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። የዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ቅድሚያ በመስጠት በዲጂታል ማንበብ እና በመማር ማስተማር ላይም ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የበይነመረብ መዳረሻን ማስፋት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ኀላፊው ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የኢንተርኔት መሠረተ ልማት ለሕዝብ ተደራሽ በኾኑ ቦታዎች እና በገጠር አካባቢዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል። የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን አቅርቦት ማመቻቸት እንደሚጠበቅም አንስተዋል። የፈጠራ ሃሳብ እና ችግር የሚፈቱ ጉዳዮች ላይ መሥራት፤ በራስ ባሕል እና ትውፊት ላይ መሠረት ያደረጉ አፕልኬሺኖችን እና ፕላትፎርሞችን በማልማት ብሎም ተግባራዊ በማድረግ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ሙያዊ ልህቀትን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።
በንድፈ ሃሳብ ደረጃ እስከ ቤተ ሙከራ ድረስ ያሉትን የትምህርት ይዘቶች በጥራት እና በተደራጀ መልኩ ለመስጠት የሚያስችሉ የሃርድ ዌር እና የሶፍትዌር መሠረተ ልማት የተሟላላቸው መማሪያ ከፍሎችን መገንባትም ይጠበቃል ብለዋል ከቴከኖሎጂው፣ ከትምህርት ሥርዓት ቀረጻው፣ ከአቅም ግንባታው፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከመሠረተ ልማት ዘርፍ የተውጣጣ ጠንካራ ግብረ ኃይል ተዘጋጅቶ እንደ ግብዓትነት የሚጠቅሙ ልምዶችን እየቀመረ ባሕልን እና እሴትን መሠረት ያደረጉ ይዘቶችን እያዘጋጀ፣ አይበገሬ እና ጠንካራ ቴክኖሎጂ መር የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቶችን መዘርጋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን