አሚኮ በሚዲያ ኢንዱስትሪው የራሱን አሻራ ያበረከተ እና አንጋፋ ባለሙያዎችን ያፈራ ተቋም ነው።

19
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ የተመሠረተበትን 30ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው።
በአሚኮ ካፕ ውድድር እየተሳተፉ የሚገኙ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋዜጠኞች አሚኮን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ የተገኙት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኛ ሳሙኤል ሞላ እንዳሉት አሚኮ በቴክኖሎጅ የተደራጀ፣ ምቹ የሥራ ከባቢ የፈጠረ ተቋም ነው። አሚኮ ባለፉት ዓመታት ይሠራቸው የነበሩ ፕሮግራሞች አስተማሪ እንደነበሩ ገልጸዋል። አሁን ላይ የዜና አቀራረቡ ተመራጭ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በቀጣይ በታጠቀው ቴክኖሎጅ ልክ አድማጭ ተመልካችን የሚመጥኑ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት በመስጠት መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የአቅም ግንባታ ሥራ ላይ ትኩረት ሠጥቶ መሥራት ይገባዋል ነው ያሉት። ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የመጡት የስፖርት ጋዜጠኛ ሀብታሙ ካሴ አሚኮ በሚዲያ ኢንዱስትሪው የራሱን አሻራ ያበረከተ፣ አንጋፋ ባለሙያዎችን ያፈራ ከሚዲያ አልፎ ትምህርት ቤት መኾኑን ገልጸዋል። የሚቀርቡ የስፖርት ዘገባዎች እና ፕሮግራሞች ተመራጭ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ከስፖርታዊ ዘገባዎች ባለፈ ክልላዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ዘገባዎች እና ፕሮግራሞችም ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።
ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የመጡት ጋዜጠኛ ሰብለ አሰፋ እንዳሉት ደግሞ አሚኮ ለሌሎች ሚዲያዎች አማራጭ የኾነ ሚዲያ ነው። ዲጂታል ዘርፋ ላይ እንደሚሠሩ የገለጹት ጋዜጠኛዋ የአሚኮ ዲጂታል ዘርፍ እያደገ የመጣ፣ ባለፉት ዓመታት ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ዘገባዎችን በመሥራት ለሌሎች ሚዲያዎች የመረጃ ምንጭ መኾኑን ገልጸዋል። ዘርፉን ይበልጥ በቴክኖሎጅ ማጠናከር እና ማኅበረሰቡ ላይ ያተኮሩ ዘገባዎችን መሥራት እንደሚገባም መክረዋል። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጋዜጠኛ መሠረት አሥማረ እንዳሉት ጉብኝቱ የአሚኮን አሠራር እና የታጠቃቸውን የሚዲያ ቴክኖሎጅ ከማስገንዘብ ባለፈ የሚዲያዎችን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ጉብኝቱ በሚዲያዎች መካከልም የልምድ ልውውጥን ለማጠናከር ያግዛል ነው ያሉት። አሚኮ ባለፉት 30 ዓመታት ፈተናዎችን አልፎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ፣ ለሌሎች ሚዲያዎች የመረጃ ምንጭ በመኾን እያገለገለ ያለ ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል። በዲጂታል፣ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በጋዜጣ የመረጃ ተደራሽነቱን ለማስፋት በዞን ከተሞች ጣብያዎች እንዲቋቋሙ ተደርጓል ብለዋል። ከክልል እና ከሀገር አቀፍ ባለፈ በመካከለኛው ምሥራቅ እና አሜሪካ ጭምር ተደራሽ ለመኾን እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህም ተቋሙ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጅ እንዲታጠቅ ተደርጓል ነው ያሉት።
ዘጋቢ :- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleአሚኮ ለጎንደር ባሕል ማዕከል ዕድገት የበኩሉን ሚና ተወጥቷል።
Next article“ሕጻናቱ የሚናፍቁሽ፣ አረጋውያን የሚጓጉልሽ”