
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከምዕተ ዓመታት በፊት ለብዙ አፍሪካውያን የባቡር አገልግሎትን ያስተዋወቀው የኢትዮጵያ ምድር ባቡር በኋላም የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎት ለረጅም ዓመታት ግዙፍ ሀብቱን ይዞ ተቀብሮ የቆየ ተቋም ነበር ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቀድማ ጀምራ ኋላ የቀረችው መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር አፍርሰው የመጀመር የመጥፎ ልማድ እስረኛ ሆና ለመቆየቷ አንዱ ማስረጃ መኾኑን ገልጸዋል። የለውጡ መንግሥት በተከተለው አዲስ ዕይታና በወሰደው እርምጃ መሠረት የሀገር አንጡራ ሀብት የሆነው ተቋም፣ ባቡር እና የባቡር መሠረተ ልማት ከተቀበረበት ጣሻ ውስጥ ተፈንቅሎ እየወጣ ለመሆኑ በግቢው የሚታዩ ነገሮች ሁሉ በገፅታቸው ይናገራሉ ብለዋል። የተደበቀው ሀብታችንን የመግለጥና የትናንት ወረትን ለሀገራዊ ብልጽግና የመጠቀም መርህን በማንገብ በተጀመሩ ሥራዎች የትራንስፖርት፣ የወርክሾፕ እና የጥገና ሥራዎች በለውጥ ሀዲድ ላይ ናቸው ነው ያሉት።
በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር ስር ያለው የድሬዳዋ ደወሌ ባቡር አገልግሎት የተበተነውን ሠራተኛ በመሰብሰብ የቆሙ ባቡሮችን ጠግኖ ወደ ሥራ በማስገባት አሁን ላይ በሳምንት ሁለት ቀን አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ለትራንስፖርት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን አገናኝቷል ብለዋል።
በመጭው ዓመትም አገልግሎቱን ከሁለት ቀናት ከፍ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ለስኬቱ የፌደራል መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። በሁሉም መስክ ራሳችንን ለመቻል የጀመርነውን ጉዞ ለማሳካት ከፍተኛ አቅም አለን። በባቡር አገልግሎት ቀድመን ጀምረን ወደኋላ መቅረታችን ቢያስቆጭም ከራሳችን አልፎ አፍሪካን በባቡር ለማስተሳሰር በአዲስ ምዕራፍ በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን