በሰሜን አሜሪካ እና ካናዳ የሚደረገውን የአጀንዳ ማሠባሠብ ሥራ ለማከናወን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

13
አዲስ አበባ: ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ወቅታዊ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ኮሚሽኑ የዲያስፖራውን ማኅበረሰብ በምክክሩ ለማሳተፍ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም በሰሜን አሜሪካ የተወካዮች ምርጫ እና የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደቱ ከነሐሴ 24/2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚጀመር ገልጸዋል። ዋና ኮሚሽነሩን ጨምሮ ስባት ኮሚሽነሮች በቦታው ተገኝተው ሂደቱን እንደሚያስተባብሩም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል። የሚሳተፉ አካላትን በተመለከተም ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች፣ ተቋማት እና ማኅበራት በምክክር ሂደቱ ይሳተፋሉ ብለዋል።
በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ዜጎች በምክክሩ እንዲሳተፉ ሲደረግ የነበረው ጥረት ውጤት ማግኘቱን እና በፍትሕ ሚኒስቴር ተቀባይነት ማግኘቱን ቃል አቀባዩ አክለዋል። በዚህም እስከ ክልል ድረስ በተዋረድ ታራሚዎች እና የፍርድ ሂደታቸውን የሚከታተሉ ዜጎችን በምክክሩ ተሳታፊ እና አጀንዳ የማሠባሠብ ሂደቱን ለማስጀመር እንቅስቃሴ ላይ መኾኑ ተገልጿል። በምክክሩ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የምሁራንን ተሳትፎ ለማሳደግ ተከታታይነት ያላቸው ውይይቶች መደረጋቸውን የገለጹት ቃል አቀባዩ የዚሁ አንድ አካል የኾነ ምሁራን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የሚያስችል ውጤታማ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ መካሄዱንም ገልጸዋል። ኮሚሽኑ በቀጣይም በእንግሊዝ፣ ስዊድን፣ በዱባይ እና ዲያስፖራውን የሚያሳትፉ ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚኖሩት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ በአካል ተንቀሳቅሶ አጀንዳ መሠብሠብ በማይችልባቸው የዓለም ሀገራትም በበየነ መረብ እና በሌሎችም አማራጮች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleመድኃኒትን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ መውሰድ ምን ሊያስከትል ይችላል ?
Next article” ከራሳችን አልፎ አፍሪካን በባቡር ለማስተሳሰር በአዲስ ምዕራፍ በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ