
ባሕር ዳር፡ ነሀሴ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሚዲያ የሰውን ልጅ የዕለት ከዕለት ሕይወት የሚነካ እና በየአንድ አንዱ እንቅስቃሴው ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው፤ ሕዝብን ከሕዝብ እና መንግሥትን ከሕዝብ ያቀራርባል፤ ዓለም አቀፍ ትብብር እና ወዳጅነትን ያጎለብታል።
የአማራ ክልል በ1985 ዓ.ም በክልሉ በነበረው የመንግሥት መዋቅር በማስታወቂያ ቢሮ ሥር የሚዲያ ሥራ ትልም ተጠነሰሰ። የሰው ኀይል የማሠባሠብም ሥራዎች ተጀመሩ፡፡ ሁለት ዓመት የፈጀ ዝግጅት ሲደርግ ከቆየ በኋላም የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ተብሎ የክልሉ ሚዲያ ተመሠረተ። ከሚዲያ አማራጮች ውስጥ ሕትመት ነበር የጅማሮ ችቦን የለኮሰው። ያኔም ነበር የአሁኗ በኩር ጋዜጣ የተወለደችው። በአሚኮ የ30 ዓመት ጉዞ ውስጥ በኩር ያለፈችበት የቴክኖሎጂ ሂደት ምን እንደሚመስል ለማስቃኘት የሕትመት ሥራ ሲጀመር ጀምሮ እስከ አሁን በጋዜጠኝነት እያገለገለ ከሚገኘው አንጋፋ ጋዜጠኛ ጌታቸው ፈንቴ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ረጅሙን የኋሊት ዘመን ዘና በሚያደርግ የጨዋታ ለዛ ሲያጫውተን ግርም፣ ትክዝ፣ ሳቅ፣ እዝን እያልን ነበር የተከታተልነው። ምክንያቱም ለሙያው የተከፈለውን መስዋዕትነት፣ እንግልት እና አድካሚ የሥራ ሂደቶች አሁን ሲታሰቡ የሚያበረታም፣ የሚያሳዝንም አለያም ፈገግ የሚያደርግም ነገር አለውና ነው። ጋዜጠኛ ጌታቸው በኵር ጋዜጣ ስትጀመር ስለ ኮምፒውተር ብዙ የሚወራበት ዘመን አልነበረም ይላል። አሁን ስናሰበው በዚህ እንዴት መሥራት ይቻላል ብለን ልንጠይቅ በምንችልባት ኮምፒውተር ያውም ያንንም መጠቀም የሚችል ሰው በመብራት ተፈልጎ በማይገኝበት ወቅት ከአዲስ አበባ ተፈልጋ በአንዲት ባለሙያ የጽሕፈት ሥራው ተጀመረ ሲል የነበረውን ሁኔታ ነግሮናል።
የዚች ጸሐፊ ስም በለጥሻቸው ሰብስቤ ነው። ከጊዜው አለመዘመን አንፃር እርሷ በጊዜው በጣም ትልቅ የኮምፒውተር ሳይንቲስት እንደማለት እንደኾነች ጠቁሟል። በእርግጥም በዛን ዘመን የዚህ ሙያ ባለቤት መኾኗ ትልቅ ነገር ነበርና ነው። ጋዜጠኛ ጌታቸው ሲያጫውተን የዘገባ ሥራዎች በጸሐፊዋ ከተተየበ በኋላ ፕሪንት ተደርጎ በአምድ እየተቆራረጠ ጋዜጣ እንዲመስል “ዳሚ” በሚባል ካርድ ላይ ይለጣጠፋል። ዳሚ የሚባለው አሁን ላይ ያሉ የጋዜጣ እና ሌይአውት ዲዛይን ሶፍትዌሮች እንደሚሠሩት አይነት ተግባር ነው ይላል።
የታተሙት ዘገባዎች በሙሉ በተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ መለጠፍ አለባቸው። በዚህ መንገድ ሁሉም ዘገባዎች “ዳሚው” ላይ ተለጥፈው ሲያበቃ ታትሞ እንደመጣ ወደ ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት አዲስ አበባ ይላክ ነበር። አንድን ዜና በጋዜጣ አሳትሞ ለንባብ ለማብቃት የሚወስደውን ጊዜ አስቡት! ሥራው አድካሚ ቢኾንም የሙያ ፍቅር እና ሥነ ምግባር ስለነበር ጋዜጠኞች ብዙም ከጉዳይ አይጽፉትም ነበር ይላል። እንዲህ አይነቱን ሂደት ተሻግራ ለሕትመት የበቃችው የመጀመሪያዋ የበኩር ጋዜጣ ዕትም 4ሺህ ቅጂዎች ነበሯት። በርዕሰ ጉዳይም የክልሉ ምክር ቤት ያደረገውን መደበኛ ጉባኤ ትዳስስ እንደነበር ያስታውሳል።
ይህ ጉዞ በሂደት እየተሻሻለ የቀለም፣ የገጽ፣ የይዘት ጥራት እና ስብጥር እየተጨመረበት አሁን ላይ ደርሷል። ጋዜጠኛው የበኩር ሕትመትን የቴክኖሎጂ ሽግግር ሲያስረዳን አሁን ላይ ባሉ የሰላም ማጣት ችግሮች ምክንያት ሕትመቶችን ማሰራጨት ባይቻልም እንኳ በድረ ገጽ እና በማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች ድንበር ሳይገድበን በኹሉም ቤት እና በኹሉም የእጅ ስልክ መድረስ ችለናል ይላል። አሁን በሳይበር አማራጭ ከመምጣታቸው ጋር አያይዞ የቀድሞው ዘመን ስለ አንድ ሰው ታሪከ ለመሥራት ብዙ መጽሐፍ፣ መጽሔት እና ጋዜጦች ማገላበጥ እና በስልክ ደውሎ መጠየቅ ግድ ይል እንደነበር ነግሮናል።
አሁን ላይ ግን በቀላሉ ኮምፒውተራችን ላይ አስሰን በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበት ጊዜ ላይ መደረሱንም ጠቁሟል። ሌላው አሚኮ በ30 ዓመት የሚዲያ ጉዞው የሚገርም የቴክኖሎጂ ሽግግር ያደረገበት ዘርፍ ደግሞ ሬዲዮ ነው። በተቋሙ የሬዲዮ ሥርጭት ሲጀመር እንደ ትልቅ የሚነሳው ቴክኖሎጂ “ሪል ቴፕ” ነው። “ሪል ቴፕ” በመጠኑ ግዙፍ የኾነ የካሴት ክር ማጫወቻ ሲኾን በወቅቱ ማራንቲዝ በሚባል ግዝፈት ባለው መቅረጸ ድምጽ በካሴት ክር ተቀርጸው የሚመጡ የድምጽ ግብዓቶች ከመጡ በኋላ የዜና ወይም የፕሮግራም ፕሮዳክሽን ለመሥራት እየተቆራረጡ እና እየተቀጠሉ የሚሠራበት መሳሪያ ነው።
የሬዲዮ ቴክኖሎጂ ላይ ያለውን ለውጥ በተመለከተ በአሚኮ ካሉት አንጋፋ የስርጭት ባለሙያ እና አሁን ላይ የሬዲዮ ሥርጭት እና ፕሮዳክሽን አስተባባሪ ኾነው እያገለገሉ ያሉት አቶ ደረጄ መኮንን በአጭሩ ነግረውናል። “በሪል ቴፕ መሥራት በጣም ከባድ፣ ጊዜን እና ጉልበትን የሚወስድ ነበር” ያሉት አስተባባሪው የአንድ ሰዓት የሬዲዮ ቅንብር ለመሥራት የሙሉ ቀን ዝግጅት ይጠይቃቸው እንደነበር ገልጸዋል። “ቀጥለው የመጡ የአናሎግ ቴክኖሎጂዎችም ብዙ ድምጽ መቀበያ፣ ማስወጫ እና የኤሌክትሪክ ኀይል ማስተላለፊያ መስመሮች የነበሩት ሲኾን አሁን ላይ ዲጂታል የኾኑ መሳሪያዎች ላይ ደርሰናል” በማለት በንጽጽር ገልጸዋል።
አሁን ላይ ያለውን የ24 ሰዓት የሬዲዮ ሥርጭት ለማዘጋጃት እና ለማሰራጨት በሰርቨር የተገናኙ ቴክኖሎጂዎች አገልግሎት ላይ ይገኛሉ።
አሁን ላይ ያሉት ቴክኖሎጅዎች “ብዙ ነገሮችን ቀላል አድርገዋል ያሉት አቶ ደረጄ “አንድ የማቀናበሪያ ኮሚፒውተር ላይ ቁጭ ብሎ የብዙ ዓመታትን ፋይል በማሰስ የምንፈልገው ይዘት ላይ ፕሮግራሞችን መሥራት ይቻላል” ሲሉ ቀላልነቱን ተናግረዋል። የአሁኑ የአሚኮ ሕትመት እና ሬዲዮ ዘርፍ የክልሉ መንግሥት የራሱን ሚዲያ ለመመሥረት በነበረው ቁርጠኛ አቋም፣ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በነበራቸው ጽናት ብሎም በሥነ ምግባር እና የሙያ ፍቅር የመጣ እንጂ የኋላዎቹ ቴክኖሎጂዎች በጣም ፈታኞች ነበሩ ብለዋል። በቴሌቪዥን እና ዲጂታል ሚዲያ ዘርፎች እንመለሳለን።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!