በበጀት ዓመቱ የሕዝብ ውክልና ኀላፊነትን ለመወጣት በትኩረት ይሠራል።

38
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዷል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በ2018 በጀት ዓመት የሕዝብ ውክልና ኀላፊነትን ለመወጣት በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ብለዋል። ያለፈውን በጀት ዓመት አፈጻጸም በመነሻነት በመውሰድ በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ ሥራ ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል። በወረዳ እና በቀበሌ ምክር ቤቶች የሚታየውን የአፈጻጸም ክፍተት በመለየት ውጤታማ ጉባኤዎችን ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል። ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ በተሻለ ቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በቀጣይም ተገቢውን የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል ሰላም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።
ሰላም፣ ልማት እና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የማይነጣጠሉ ጉዳዮች በመኾናቸው በተዋረድ ያሉት ምክር ቤቶች በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። በአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሀናን አብዱ በበጀት ዓመቱ የተዋረድ ምክር ቤቶችን የመደገፍ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል። የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታትም የተሻለ ሥራ ለመሥራት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በወረዳ ምክር ቤቶች የእቅድ ትውውቅ በማካሄድ የምክር ቤቶችን ዋና ዋና ተግባራት ለማከናዎን እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የእቅዱ አንዱ አካል ሰላምን ማረጋገጥ መኾኑን ነው የተናገሩት። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አፈ ጉባኤ አድና ምሕረቱ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክር ቤት በኩል የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለመጠበቅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። በሚደረጉ ጉባኤዎች ሰላምን ለማስፈን ጠንካራ የውሳኔ ሀሳቦችን በማሳለፍ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አፈ ጉባኤ ጌትነት እውነቱ በ2018 በጀት ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እንዲሠሩ ይደረጋል ብለዋል። የአሥፈጻሚው አካል በምክር ቤቱ የጸደቀውን በጀት ለታቀደው ዓላማ መዋሉን በማረጋገጥ ቁጥጥር እንደሚደረግ ነው የተናገሩት። የአፈጻጸም ክፍተቶች ሲገኙም ለማስተካከል ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት። ልማት እንዲጠናከር፣ የሕዝቡ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ እና የተሻለ ሰላም እንዲመጣ በትኩረት እንደሚሠራም ተመላክቷል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየትውልዱ አደራ!
Next articleየኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኮምቦልቻ ከተማ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታን አስጀመረ።