
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልእክት ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚያጠናክሩ፣ የኢትዮጵያን ማንሠራራት የሚያበሥሩ አያሌ ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክቶችን እያስጀመርን እንጨርሳለን፤ እየገነባን ሀገርን ወደ ልዕልና እናሻግራለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ አብሳሪ የኾነውን የሚኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን ዛሬ በይፋ አስጀምረናል ብለዋል።
144 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የፍጥነት መንገዱ መሠረተ ልማትን ለማዘመን እና የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማሳካት የተያዘውን ግልፅ ራዕይ እና ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቅ እንደኾነ ጠቁመዋል።የፍጥነት መንገዱ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎችን እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን በማስተሳሰር የሕዝቦችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብር የሚያጎለብት ህያው የአብሮነት እና የጋራ ዕድገት ምልክት ነው ብለውታል።
ከወደብ እስከ ማዕከላዊ የሀገራችን ክፍል ያለውን የትራንስፖርት ወጪ እና ጊዜን በመቆጠብ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የገበያ ተደራሽነታችንን እና ተወዳዳሪነታችንን በእጅጉ ያሳድጋል። የሚኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ በጥራት እና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በግንባታው የሚሳተፉ አካላት ኀላፊነታቸውን በዲሲፕሊን እንዲወጡ አደራ እያልኩ ለፕሮጀክቱ መሳካት ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!