መንግሥት የመንግሥት ሠራተኞችን የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል የሚያስችል አዳዲስ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታወቀ።

473
ባሕር ዳር: ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችን ጨምሮ የመንግሥት ሠራተኞችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችል አዳዲስ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታውቋል።
የደመወዝ እና የግብር ማሻሻያ የተደረገባቸውም ፡-
✍️የዝቅተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከ 4ሺህ 760 ብር ወደ 6ሺህ ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል።
✍️ከፍተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከ 21ሺህ 492 ብር ወደ 39ሺህ እንዲያድግ ተወስኗል።
✍️አዲስ ለሚቀጠሩ የዲግሪ ተመራቂዎች የመነሻ ደመወዝ ከ 6ሺህ 940 ብር ወደ 11ሺህ 500 ብር ከፍ ብሏል።ከዚህ በፊት 600 ብር የነበረው ከታክስ ነጻ የኾነ ገቢ መጠን ወደ 2ሺህ ብር ከፍ ብሏል። ይህ ለሁሉም አይነት ተቀጣሪዎች የሚሠራ ነው።መንግሥት የኢኮኖሚ ሪፎርም በማድረግ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እና የሀገርን ኢኮኖሚ ለማጠናከር እየሠራ ነው። ይህ የደመወዝ እና የግብር ማሻሻያ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ከኢኮኖሚው ዕድገት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ታስቦ የተደረገ ነው ብሏል።
ይህ አዲስ የደመወዝ ጭማሪ ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚኾን ሲኾን ለዚህ ማሻሻያ ከ160 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ስለመመደቡም ተብራርቷል። ይህም ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ የሚወጣውን አጠቃላይ ዓመታዊ ወጭ ወደ 560 ቢሊዮን ብር ያደርሰዋል።መንግሥት በቀጣይ የቤት አቅርቦትን እና የጤና መድህንን ጨምሮ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ለማሻሻል ዕቅድ መኖሩም ነው የተገለጸው።
መንግሥት የዜጎችን ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም በተገቢው ደረጃ ለመክፈል የሚያስችል ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጠንካራ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጠቁሟል፡፡ ይህንን ለማሳካትም የመንግሥት ሠራተኞች በየመስካቸው ውጤታማ በመኾን እና ሙስናን በመታገል የኢኮኖሚውን ዕድገት እንዲያግዙ ጥሪ ቀርቧል። ይህም የሀገርን የግብር ገቢ ለማሳደግ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረትን ለማጠናከር ወሳኝ መኾኑ ተገልጿል።እንደ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መረጃ መንግሥት እስካሁን ለሀገር ዕድገት እና ብልጽግና ሲሉ ዝቅተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው በትጋት እየሠሩ ላሉ የመንግሥት ሠራተኞች ምሥጋና አቅርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleችግሮች በሀገራዊ ምክክር ሂደት እንዲፈቱ የሴቶች አስተዋጽኦ የላቀ ነው።
Next article“መንግሥት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሀገር ዐቅም የሚፈቅደውን ርምጃ እየወሰደ ነው” ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን