
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በትንሹ ጀመረ፣ በረጅሙ አማተረ። በጥበብ ተመራ፤ በብርታት ሠራ። በሥራው ከዕድሜው አለፈ፤ በበርታቱ ከፍ ብሎ ገዘፈ።
ታላላቆቹን ቀድሟቸዋል፣ ታናናሾቹን ርቋቸዋል። ታላላቆቹ ለምዕተ ዓመት የተጓዙትን፣ ተጉዘውም ያልደረሱበትን በ30 ዓመታት ተሻግሮታል። ዛሬ ከፊት ኾኖ ያስከትላቸዋል። እየቀደመ ይመራቸዋል። እያለፈ መንገድ ያሳያቸዋል። እያፈራ ይመግባቸዋል። እያመነጨ ያጠጣቸዋል። ለብዙዎች ቤታቸው፣ ለዕልፍ አዕላፋት መናገሪያ አንደበታቸው፣ መጻፊያ ብዕራቸው፣ መከተቢያ ብራናቸው፣ መሻገሪያ ድልድያቸው፣ መታያ መስታውታቸው ነው። ብዙዎች ከመክሊታቸው ጋር ተገናኝተውበታል። ሕልማቸውን ኖረውበታል። የሕይዎታቸውን መሠረት ጥለውበታል።
ለዘመናት ያልታዩት ታይተውበታል። ለዘመናት ያልተገለጡት ተገልጠውበታል። እውነታቸውን ነግረውበታል፣ ማንነታቸውን አሳይተውበታል፣ ታሪካቸውን አስተዋውቀውበታል። ተስፋቸውን ገልጸውበታል፣ ምኞታቸውን እውን አድርገውበታል። በ30 ዓመታት በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ አሳርፏል። የደመቀ ታሪክ፣ በደመቀ ቀለም ጽፏል አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን። በጉዞው የተነሱ ወጀቦች አላናወጹትም። ፈተናዎች መስመሩን አላሳቱትም። በጽናት በውቅያኖሱ ላይ መርከቡን አስተካክሎ ተጓዘ እንጂ።
ሠራተኞቹ እንደዛሬው ሚዲያ በእጅ ባልተያዘበት፣ በኪስ ተይዞ ባልተዞረበት፣ የተመቸ መንገድ ባልተሠራበት፣ በበይነ መረብ በማይታወቅበት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሕልም በኾነበት ዘመን በእጅ እና በእግራቸው እየቧጠጡ ተራራዎችን ወጥተዋል፣ አስቸጋሪ ቁልቁለቶችን ወርደዋል፣ ማዕበል የሚያናውጠው ወንዝ ተሻግረዋል፣ ውኃ በሌለበት በረሃ ተጉዘዋል።
መዝሙር ሐዋዝ የብዙኃን መገናኛ ዕድገት በኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው ለአሚኮ መሠረት የኾነችው በኩር ጋዜጣ ናት ይላሉ። በክልላዊ የብዙኀን መገናኛ አውታሮች በኩል በኩር ጋዜጣን የሚቀድም የለም። ይህም በኢትዮጵያ በክልላዊ የብዙኀን መገናኛ አውታሮች አሚኮ ቀዳሚው ነው ማለት ነው። በኩር ብሎ ብኩርናውን የጀመረው አሚኮ በ30 ዓመታት እውን በዚህ የጎልማሳነት ዕድሜ ይሄን ማድረግ ይቻላልን ? የሚያስብል ሥራ ሠርቷል። ከጥንቶቹ ቀድሟል። ከተከታዮቹ ርቋልና።
በታኅሳስ 7/1987 ዓ.ም በበኩር ጋዜጣ በስምንት ገጾች አሀዱ ብሎ ሥራውን የጀመረው አሚኮ ዛሬ ኢትዮጵያ ካሏት ግዙፍ የሚዲያ ተቋማት አንደኛው እና የትኩረት ማዕከል ነው። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጋዜጠኛ መሠረት አስማረ አሚኮ ታላቅ እንደሚኾን ራዕይ የሰነቁ ባለ ራዕዮች ያቋቋሙት ነው ይላሉ። አሚኮ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በታሪክ ሁለተኛውን የራዲዮ፣ የቴሌቪዥን፣ የኤፍኤም ጣቢያዎችን የመሠረተ ታላቅ ተቋም ነው። አሚኮ በታሪክ ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው የክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ ለሚዲያ ያላቸው መሻት ወሳኝነት ነበረው ነው የሚሉት።
አንድ ለእናቱ ከነበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ የአየር ሰዓት የነበረው አሚኮ በጥቂት ጀምሮ በሰፊው ይሠራ ነበርና ዛሬ ላይ ግዙፉ ተቋም ኾኗል። አስቀድሞ ገና ለሕዝብ ማንነት፣ እሴት፣ ሃይማኖት እና ታሪክ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው አሚኮ ሳምንት ጠብቃ በምትሰጠው 30 ደቂቃ አዲስ ነገርን ለሕዝብ አስተዋውቋል። ለአብነት የአውራምባ ማኅበረሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው በዚያች 30 ደቂቃ የአየር ሰዓት በአሚኮ አማካኝነት ነበር ነው ያሉት።
ሳምንት ጠብቃ በምትመጣ የ30 ደቂቃ የአየር ሰዓት የሚያስደንቁ እውነታዎችን የገለጠው አሚኮ ከ30 ደቂቃ እስከ 30 ዓመታት ተጉዟል። ጉዞው ሩቅ እና ረቂቅ ነውና ይቀጥላል። አሚኮ ለሕዝብ ባሕል፣ እሴት፣ ወግ፣ ማኅበራዊ ስሪት የሚሰጠው ትኩረት ልዩ ነው። የጥንቱን ያስጠብቃል። ያልታየውን ይገልጣል። የታየውን ያዳብራል።
ዋና መቀመጫውን የክልልሉ ርዕሰ ከተማ ባሕርዳር ያደረገው አሚኮ የ30 ደቂቃዋን የአየር ሰዓት ለመጠቀም የአሚኮ ሠራተኞች አያሌ ውጣ ውረዶችን ያሳልፉ ነበር። ተንቀሳቃሽ ምስሉን በካሴት ቀርጸው ወደ መናኸሪያ ያቀናሉ። በዚያም ለተሳፋሪ ወይም ለአሽከርካሪ ይልካሉ። ታዲያ ይህ ሁልጊዜ ተሟልቶ ላይደርስ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ መኪናው መንገድ ላይ ያድርና ጊዜው ያልፋል። ካለበለዚያ ካሴቱም ሊጠፋ ይችላል ነው የሚሉት።
ባለራዕዮቹ የአሚኮ ሠራተኞች ግን ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ ከሥራ አልገታቸውም። ይልቅስ የተሻለ ነገ እንዲኖር አተጋቸው እንጂ። መዝሙር ሐዋዝ ሲጽፉ ድርጅቱ በራሱ መንገድ ዘገባዎችን እያቀናበረ ወደ ኢትዮጵያ ራዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና ወደ ሌሎች ተቋማት ቢልክም ተቋማቱ በነበራቸው የአየር ሰዓት እና የጋዜጣ ገጽ ውስንነት ምክንያት ዘገባዎችን ተቀብለው ለማስተናገድ ፈተና ይገጥማቸው ነበር። የኅብረተሰቡን የመረጃ ፍላጎት ማደግ ተከትሎ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮችን በብዙኀን መገናኛ ጉልበት በመታገዝ ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑን የተገነዘበው የአማራ ክልል መንግሥት የብዙኀን መገናኛ አውታሩ የሚስፋፋበትን አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ተግባር ገባ። በዚህም ምክንያት የአማራ ድምጽ የተሰኘው የአማራ ራዲዮ ተመሠረተ። ይህም ዘመን ግንቦት 16/1989 ዓ.ም ነበር። ከዚያም ቴሌቪዥን ተከተለ።
አሚኮ የራሱ ሥፍራ ተሰጥቶት መለስተኛ ሕንጻ ገንብቶ ሥራውን ጀመረ። በዚያ ዘመን የተሟላ ቢሮ፣ ጋዜጠኖች የሚቀመጡበት ወንበር አልነበረም። የተጣበበ እና የማይመች ነበር። በዜና ጉባኤ በዛፍ ሥር ይቀመጡ ነበር። እንዲህም ኾኖ ግን የአሚኮ ሠራተኞች ነገን እያሰቡ በሙያዊ ፍቅር እና በሙያዊ ሥነ ምግባር በብርታት ሠሩ። ነገን የተሻለ ለማድረግ ታተሩ። በብርታታቸውም የአሚኮን ነገዎች አሳመሩ። በበኩር ጋዜጣ በስምንት ገጾች የጀመረው፣ በ30 ደቂቃ በሳምንት ሲታይ፣ በአንድ ቋንቋ ብቻ ሲያስተላልፍ የነበረው አሚኮ አሁን ላይ ልሳነ ብዙ በኾነችው ኢትዮጵያ በ12 ቋንቋዎች ያስተላልፋል፣ አሚኮ አሁን ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ አራት ጋዜጦች፣ ሰባት የራዲዮ ጣቢያዎች አሉት። ለ24 ሰዓታት ሳያቋርጥ ያሰራጫል።
ምን ይህ ብቻ የካሴት ክር በመቀስ ከመቁረጥ ተነስቶ አሁን ላይ ተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ እስከመገንባት ደርሷል። በሳምንት በ30 ደቂቃ ከማስተላለፍ ተነስቶ አሁን ላይ በዲጂታል ሚዲያ በየሰከንዶች እና በየደቂቃዎች መረጃዎችን ለዓለም ያዳርሳል። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጋዜጠኛ መሠረት አስማረ እንደሚሉት አሚኮ በክልሉ ለሚገኙ የብሔረሰብ ቋንቋዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ሠርቷል ይላሉ። በዚህም ቋንቋዎች እንዲያድጉ፣ እንዲተዋወቁ፣ የሥነ ጽሑፍ አድማሳቸው እንዲሰፋ፣ የተደራሽነት መጠናቸው እንዲገዝፍ አድርጓል ።
አሚኮ በ30 ዓመታት ጉዞው በኅብረተሰብ ውስጥ ሁሉም አይነት ለውጥ እንዲመጣ ሠርቷል። ምርታማነታቸው ያደገ አርሶ አደሮች፣ ንግዳቸው የዘመነ ነጋዴዎች፣ በሃሳብ የበላይነት የሚያምኑ ፖለቲከኞች፣ ነገን የሚያሳምሩ ተወዳዳሪ ተማሪዎች፣ ጤናቸው የተጠበቀ ዜጎች፣ ዘመኑን የዋጁ ተመራማሪዎች፣ ሕዝብን በቅንነት የሚያገለግሉ ሠራተኞች፣ ለትውልድ ጥሪት የሚተው መሪዎች እንዲፈጠሩ በትጋት አገልግሏል። መፍትሔም አመላክቷል።
የኢትዮጵያን ትናንት፣ ዛሬን እና ነገዋን አስተሳስሯል። አሚኮ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በመልካም መንፈስ ቃኝቷል። አዲስ የፖለቲካ ባሕል እንዲፈጠር መንገድ አሳይቷል። አሚኮ ንቃተ ሕሊናው ላቅ ያለ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የድርሻውን ተወጥቷል። አሚኮ የአማራ ክልል እና የኢትዮጵያን እምቅ ሀብቶች አስተዋውቋል።
አሚኮ ልደትን በላሊበላ በተሰኘ ዝግጅቱ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላን ድንቅ ሥራ ለዓለም አስተዋውቋል። በማሜ ጋሪያ የሚቀርበውን ቤዛ ኩሉን በቀጥታ እያሳየ በሰዎች ልብ ላይ አትሟል። የጎንደርን ጥምቀት በዓለሙ ሁሉ እንዲናኝ አድርጓል። የግሸንን ታሪክ እንዳረፈበት ተራራ ከፍ አድርጎ ለዓለሙ አሳይቷል። የአገው ፈረሰኞችን አድምቋል፣ ደብረ ታቦርን በደብረታቦር አስተዋውቋል። አሚኮ ያልገለጣቸው ታሪኮች፣ ያላሳያቸው እሴቶች፣ ያልነገራቸው ባሕሎች የሉም። ቤዛ ኩሉ ከማሜ ጋሪያ ላይ ኾኖ ለዓለም ገዝፎ የታየው በአሚኮ ነው። ሌሎችም ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች የደመቁት፣ በሰው ልብ ላይ የተጻፉት በአሚኮ አማካኝነት ነው።
አሚኮ ያልተገለጠውን እየገለጠ፣ ያልተደረሰበትን እየደረሰ፣ ያልተነገረውን እየነገረ በሕዝብ ልብ ውስጥ መልካም ነገር ጽፏል። እርሱም በታሪክ ላይ ደማቅ ታሪኩን አጽፏል። ሀገር እና ሕዝብ አደጋ በገጠማቸው ጊዜ መፍትሔ አመላክቷል። ሀገር እና ሕዝብ ጸንተው እንዲኖሩ ጸንቷል ነው የሚሉት። ጋዜጠኛ መሠረት እንደሚሉት የአሚኮ የዕድገት ፍጥነት መሠረቱ የክልሉ መሪዎች እና ሕዝብ ለሚዲያ ያላቸው ቀናኢነት፣ የአሚኮ መሪዎች እና ሠራተኞች ብልሃት እና በዓላማ መጽናት ነው። የአሚኮ መሪዎች በቤቱ ያደጉ፣ የሙያ ሥነ ምግባሩን እና ባሕሉን የሚረዱ፣ ሠራተኞቹ ችግርን ተቋቁመው የሚሠሩ መኾናቸው እድገቱን ፈጣን እንዲኾን አድርጎታል ነው የሚሉት።
አሚኮ የራሱን ባሕል፣ ቀለም፣ ለዛ ይዞ የኖረ፣ ራሱን ከዘመኑ ጋር ያዘመነ፣ ለሃሳብ የበላይነት ቅደሚያ የሚሰጥ፣ የንግግር ባሕልን የሚያዳብር፣ እውነትን ተናግሮ ከመሸበት ማደር በሚል ማኅበረሰብ ውስጥ እንደተመሠረተ ሚዲያ እውነትን መሠረት ያደረገ ነው ይላሉ። አሚኮ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን፣ ለኢትዮጵያ ክብር እና አንድነት የሚሠራ፣ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ቀዬ የሚደርስ፣ ስለ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚያገባው እና ስለ እነርሱ መለወጥ የሚሠራ ከኢትዮጵያ ተሻግሮ ለዓለም ተደራሽ እየኾነ ያለ ነው።
አሚኮ ሰው ነው የሚሉት ጋዜጠኛ መሠረት በርካታ ሠራተኞችን በማሠልጠን ለኢትዮጵያ የሚዲያ ተቋማት አበርክቷል። አሚኮ የጋዜጠኝነት ሥልጠና ማዕከል ነው፣ ለኢትዮጵያ ሚዲያ የጋዜጠኝነት መፈልፈያ ነውና ይላሉ። አሚኮ የሰው ኀይል ላይ በመሥራቱ አስደናቂ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ጸሐፊዎችን፣ አቀናባሪዎችን፣ ቀራጮችን እና ሌሎች ባለሙያዎችን አፍርቷል ነው የሚሉት። በ30 ዓመታት ጉዞው አያሌ ፈተናዎችን ያለፈው፣ ከዕድሜው የገዘፈ ታሪክ የጻፈው አሚኮ የ30ኛ ዓመት የጎልማሳነት ዘመኑን እያከበረ ነው። በ30ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ የትናንቱን ይዘክራል። የነገውን መንገድ ያሰምራል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!