የበጎ አድራጎት ሥራዎች ባሕል እየኾኑ ነው።  

17

ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ መሪዎች እና ሠራተኞች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል፡፡ በባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ጋር በመተባበር በባሕር ዳር ከተማ ለሚገኘው ዝግባ የሕጻናት እና አረጋውያን መርጃ ድርጅት የአልባሳት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) በክልሉ ያሉ ተቋማት በክረምት የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን እያከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ የሥራና ሥልጠና ቢሮ የዚሁ አካል የኾነውን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ እና አረጋውያንን የመደገፍ ሥራ መሥራታቸው የሚበረታታ ተግባር መኾኑን አንስተዋል፡፡ በዚህ ዓመት እየተሠራ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሁሉንም አቅሞች በማቀናጀት ያቀናጀ እንደኾነ ገልጸዋል። በጎ ፈቃድን ባሕል ለማድረግ ያለመ ሂደት ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) የቢሮው መሪዎች እና ሠራተኞች ዛሬ የተከሉትን ችግኞች በመከታተል እንደሚንከባከቡ ገልጸዋል፡፡ ቢሮው የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በየዓመቱ በማከናወን ሕጻናት እና አረጋውያን መደገፍ ባሕል ያደረገው ተግባር ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ዓመትም የቢሮው ሠራተኞች ከባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ለዝግባ የሕጻናትና አረጋውያን መርጃ ድርጅት የአልባሳት ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ችግኝ ለመትከል ሲታሰብ ባለፈው ዓመት የተተከሉትን መንከባከብን አብሮ ለመሥራት በዕቅድ መያዙን የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አማረ ዓለሙ ገልጸዋል፡፡ እንደ ክልል በሚገኙ በሁሉም ኮሌጆች የችግኝ ተከላን ጨምሮ በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ክልል አረንጓዴ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መኾኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መካከል የአረጋውያንን ቤት መሥራት በክልሉ የሚገኙ 42 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች እያንዳንዳቸው አንድ የአቅመ ደካሞችን ቤት እንዲገነቡ ዕቅድ ተይዞ እስካሁን 42 ቤቶች መሠራታቸውን ገልጸዋል። በቢሮውም የአቅመ ደካማ ቤት ለመሥራት ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

ከሌማት ትሩፋት በኮሌጆች የሚመረቱ የግብርና ምርቶችን ለአቅመ ደካሞች የማጋራት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በኮሌጆች በልብስ ስፌት ትምህርት ክፍል የሚሠሩ ልብሶችን ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ይደግፋሉ፤ ዛሬም በባሕርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የተሠሩትን ለአረጋውያን አስረክበናል ነው ያሉት፡፡

በዝግባ የሕጻናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ያገኘናቸው ሃምሳ አለቃ ሽፈራው መንግሥቱ በተደረገላቸው የአልባሳት ድጋፍ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የሚኖሩት እማሆይ ወርቄ በላይ በተደረገው ድጋፍ ደስታቸው ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

እንኳን ድጋፍ ሲደረግ እንዲሁ መጎብኘት ለእነሱ ደስታ የሚሰጣቸው መኾኑን ገልጸዋል። ፡ የድርጅቱ ሥራ አሥኪያጅ ስለሽ ጌታቸው ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል። ሌሎች ተቋማት እና ግለሰቦችም በሚችሉት ሁሉ ሕጻናትና አረጋውያንን እንዲደግፉ መልዕክት አስተላለፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበበጀት ዓመቱ ከ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ የቤተሰብ አባላት የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ኾነዋል።
Next article“ድጋፉ ከኔ አልፎ ደብተር በምን ልግዛላት የሚለውን የእናቴን ጭንቀት ያቀለለ ነው” ድጋፍ የተደረገላት ተማሪ