ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ግብርና በአፍሪካ። 

34

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ግብርና በአፍሪካ ከ60 በመቶ በላይ ለሚኾነን ሕዝብ የሥራ ዕድል የፈጠረ እና ለአህጉሩ ጠቅላላ የውስጥ ምርት 23 በመቶ አስተዋጽዖ የሚያበረክት ነው። የአየር ንብረት ለውጥ፣ ደካማ የኾነ የገበያ ሰንስለት፣ የምርታማነት ማነስ እና በምርት መሠብሠብ ወቅት የሚኖር ብክነት ዘርፋን እየፈተነው ይገኛል።

በአፍሪካ የግብርና ልማት ዘርፉን የሚያዘምን እና የሚያሳድግ ቴክኖሎጂ ፍላጎት እያደገ ባለበት ወቅት የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ዕድሎችን ይዞ ብቅ ብሏል ሲል አፍሪካን ሊደርሺፕ ማጋዚን በድረ ገጹ አስነብቧል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰብል ምርታማነት ግመታ፣ የመሥኖ ልማት አሥተዳደር፣ የአፈር ይዘት እና የሰብል ቁጥጥር ላይ ቀድሞ መረጃን በመስጠት ዘርፉን በስፋት ማገዝ ጀምሯል።

የግብርና ትንበያ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎች የአፍሪካ አርሶ አደሮች ሊኖር የሚችልን የአየር ንብረት ለውጥ ቀድመው በመረዳት በግብርና ሥራቸው ላይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲወስኑ ይረዳቸዋል::

ለአብነት በኬንያ ታናናሽ የእርሻ ይዞታዎች ላይ ተግባራዊ የተደረገው የአይ.ቢ.ኤም ኩባንያው “ዋትሰን” የተሰኘ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዘ የግብርና መረጃ ሥርዓት ለአርሶ አደሮች የስልክ መልዕክት በመላክ ምን አይነት የግብርና ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ይጠቁማቸዋል።

በሩዋንዳ ተግባራዊ የተደረገው “አግሪጎ” የተሰኘ መተግበሪያ ደግሞ በአፈር ውስጥ ያለን የእርጥበት እና ማዳበሪያ መጠን በመመርመር አርሶ አደሮቹ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲወስኑ እያገዝ ይገኛል።

በናይጄሪያ ዜንቨስ የተሰኘ በግብርና ቴክኖሎጂ ላይ የተሰማራ ድርጅት የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ምሳሌ የኾነ ውጤትን ማግኘቱን አፍሪካን ሊደርሺፕ ማጋዚን አስነብቧል::

ይህ ድርጅት ሥራ ላይ ያዋለው ቴክኖሎጂ የአፈርን እርጥበት፣ የሙቀት መጠን እና በአፈር ውስጥ ያለውን የማዕድን መጠን በመመርመር መረጃን የሚያደርስ ነው።

ቴክኖሎጂው በተመረጡ የሙከራ ጣቢያዎች የምርት ብክነትን ቀንሷል:: ምርታማነትንም ከ20 በመቶ በላይ አሳድጓል::

የገበያ መረጃ፣ የአየር ንብረት ትንበያ እና ተሞክሮ የሚኾኑ የግብርና ልምዶችን በራሳቸው ቋንቋ ለአርሶ አደሮቹ የሚያደርስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታማነትን ያሳደገችው ሀገር ደግሞ ጋና ናት።

1 ነጥብ 7 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ በመኾን ምርታማነታቸውን እስከ 30 በመቶ ከፍ ማድረግ ችለዋል::

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ለግብርናው ዘርፍ ተስፋን የሰጠ ቢኾንም በአፍሪካ ያለው የመረጃ መረብ ትስስር ችግር፣ የኤሌክትሪክ ኀይል በሁሉም ስፍራ አለመኖር እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቁሳቁሶች ዋጋ ውድነት አሁንም ፈተናዎች ናቸው።

ምንጭ፦ አፍሪካን ሊደርሽፕሜጋዚን ዶት ሲኦ ዶት ዩኬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአሚኮ ሰላም እና አብሮነት እንዲጎለብት ከፍተኛ ድርሻ እየተወጣ ነው።
Next articleማርን በባሕላዊ መንገድ እስከ መቼ?